ወላይታ ድቻ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

የቅድመ ውድድር ዝግጀታቸውን ከጀመሩ ሁለት ሳምንታት ያለፋቸው የጦና ንቦቹ ሁለት ተጫዋቾችን የግላቸው አድርገዋል፡፡

የመሐል ተከላካዩ አዩብ በቀታ ለወላይታ ድቻ የፈረመ ተጫዋች ነው፡፡ በሀዲያ ሆሳዕና በተሰረዘው የውድድር ዓመት በግሉ መልካም ጊዜ የነበረው ይህ ተጫዋች ባለፈው ወር ለከፍተኛ ሊጉ ክለብ አርባምንጭ ከተማ ለመጫወት ስምምነት ፈፅሞ የነበረ ቢሆንም ምርጫውን ወላይታ ድቻ በማድረግ የሁለት ዓመት ውል ፈርሟል፡፡

ሌላኛው ክለቡን የተቀላቀለው ወጣቱ አማካይ አብነት ይግለጡ ነው፡፡ ከመከላከያ ወጣት ቡድን ተገኝቶ 2011 ወደ ዋናው ቡድን አድጎ መጫወት የቻለው አብነት የተሰረዘውን የ2012 የውድድር ዘመን በደቡብ ፖሊስ በመጫወት ከቆየ በኃላ ወደ ወላይታ ድቻ በሁለት ዓመት ውል አምርቷል፡፡

©ሶከር ኢትዮጵያ