​ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ ከምድቡ ተሰናበተ

በታንዛኒያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚዎችን ዛሬ ሲያሳውቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከምድብ መሰናበቱ ተረጋግጧል።

በአሠልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከኬንያ እና ሱዳን ጋር ተደልድሎ ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን ማከናወኑ ይታወሳል። ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታም በኬንያ ሦስት ለምንም የረታ ሲሆን በሁለተኛው ጨዋታ ግን ከመመራት ተነስቶ ሦስት ለሁለት በሆነ ውጤት አሸንፏል። 

በውድድሩ ደንብ መሠረት የየምድቦቹ አንደኞች ግማሽ ፍፃሜውን በቀጥታ ሲቀላቀሉ ካሉት ሦስት ምድቦች ጥሩ ሁለተኛ የተባለው አንድ ቡድን መሪዎቹን ተከትሎ ወደ አራቱ ውስጥ ይገባል። ይህንን ተከትሎ ብሔራዊ ቡድኑ የምድቡ አንደኛ የሚሆንበትን ዕድል በኬኒያ ቢነጠቅም ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ የብሩንዲን እና ደቡብ ሱዳንን ጨዋታ ሲጠባበቅ ነበር። በዚህ ጨዋታ ደቡብ ሱዳን በብሩንዲ ብትረታ ቡድኑ በቀጥታ ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ ወደ ቀጣይ ዙር የሚያልፍ ቢሆንም ደቡብ ሱዳን ጨዋታውን አራት ለምንም አሸንፋለች። ውጤቱን ተከትሎም ደቡብ ሱዳን ምርጥ ሁለተኛ ሆና ወደ ቀጣይ ዙር አልፋለች።

ከደቂቃዎች በፊት በተጠናቀቀው ጨዋታም የምድቡ መሪ ኬንያ ሱዳን ላይ በፎርቹን ኦሞቶ እና ቤንሰን ኦቺንጎ አማካኝነት ባስቆጠረችው ሁለት ጎሎች አሸንፋለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም ከሦስቱ ምድቦች ውስጥ የተሻለ ነጥብ እና የግብ ልዩነት ያገኘችው ደቡብ ሱዳን የየምድቦቹ አንደኛ ሆነው ያጠናቀቁትን ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ እና ኬንያን ተከትላ አራት ውስጥ ገብታለች። በግማሽ ፍፃሜም ዩጋንዳ ከኬንያ እንዲሁም ታንዛኒያ ከደቡብ ሱዳን የሚጫወቱ ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ