​የሴቶች እግርኳስ ገፅ | ቆይታ ከአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ ጋር

በ1990ዎቹ አጋማሽ የሴቶች እግርኳስ በተፋፋመበት ወቅት በአሰልጣኝነት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ካደረጉ አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆነው ያሬድ ቶሌራ የዛሬው የሴቶች ገፅ ዕንግዳችን ነው።

በቅርብ ዓመታት ከአንደኛ ሊጉ ወደ ከፍተኛ ሊግ አሳድጎት ጥሩ ተፎካካሪ ባደረገው ለገጣፎ ለገዳዲ እንዲሁም በወልቂጤ እና መድን ውስጥ በሠራቸው ቡድኖች ይበልጥ ይታወቃል። በተለያዩ ወቅቶች ከአሰልጣኝ ሥዩም አባተ፣ ገብረመድኅን ኃይሌ እና ውበቱ አባተ ጋር አብሮ በመሥራት ልምድን ያካበተ፣ በወጣቶች እግርኳስም በመድን እና ደደቢት ታዳጊ ቡድኖች ውስጥ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ 17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ድረስ ቆይታን ያደረገ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ የደሴ ከተማ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተሹሟል። ታድያ ከሚሊኒየሙ መጀመርያ ወዲህ በወንዶች እግርኳስ በዚህ መልኩ ይቆይ እንጂ ከዚያ አስቀድሞ አሰልጣኝነትን የጀመረው በሴቶች እግርኳስ የነበር መሆኑ የዛሬው የሴቶች ገፅ ዕንግዳችን እንዲሆን መነሻ ሆኗል፤ አሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ (ድሬ)።

የጃንሜዳ ልጅ የሆነው ያሬድ በታዳጊነት ዘመኑ ጃን ሜዳ አካባቢ በዞን አራት ሥር ይደረግ በነበረው ውድድር በአሰልጣኝ አዕምሮ ቦጋለ በሚያሰለጥነው ቡድን እንዲሁም በቅድስተማርያም ውስጥ መጫወት ጀምሮ በመቀጠል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የ’ሲ’ እና የ’ቢ’ ቡድኖች ውስጥ አሳልፏል። በልጅነቱ ከእግርኳስ ጋር በዚህ መንገድ ያስተዋወቀው ሰፈሩ ጃንሜዳ በተመሳሳይ ሁኔታ አሁንም ድረስ እህል ውሀው ወደሆነው የአሰልጣኝነት ህይወት እንዲገባም በር ከፍቶለታል። አጀማመሩም ለሙያው በነበረው ፍላጎት በራሱ ተነሳሽነት ‘ድሬ እና ልጆቹ’ በሚባል እነአሉላ ግርማ እና ሙሉጌታ አሰፋን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ባፈራ የህፃናት ቡድንን በማሰልጠን ነበር። ከዚህ በመቀጠል 1993 ላይ አዲስ ኮከብ የሚባል የሴቶች ቡድን ያቀረበለትን ጥያቄ በመቀበል ለአምስት ዓመታት ከቡድኑ ጋር በመስራት የሴቶች እግርኳስ የለውጥ ዘመን አንድ አካል ለመሆን በቅቷል።

የኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ ጃንሜዳ ላይ በጥቂት ቡድኖች መካከል ከሚደረግ ውድድር ጀምሮ የበርካታ ክለቦች እና የብሔራዊ ቡድን ምስረታ እንዲሁም የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ዓይነት ከፍ ያሉ ዕድገቶችን ያስመዘገበባቸው እነዛ ተከታታይ ዓመታት በእርግጥም ወሳኝ ነበሩ። ለያሬድ የያኔው የተጫዋቾች ጠንካራ መንፈስ እና የጨዋታቸው ሳቢነት እስከአሁንም እንደሚያስገርመው ይገልፃል።  “ሁሉም በበጎ ፍቃደኝነት ነበር የሚሰራው። ተጫዋቾቹም ከለገሀር ፣ ከአስኮ ፣ ከሳሪስ ፣ ከአየር ጤና ከተለያዩ ቦታዎች ነበር የሚመጡት። የምግብ እና የትራንስፖርት ሌላው ቀርቶ የመጫወቻ ጫማ እንኳን አልነበራቸውም። በመሀላቸው የነበረው ፍቅር ግን በጣም የተለየ ነበር። ተጫውተው ሲጨርሱ ያላቸውን አዋጥተው ሻወር ይወስዳሉ ፣ ምግብ ይበላሉ። ፍቅራቸውን ለመግለፅ ቃላቶች ያጥሩኛል። ምርጥ እግርኳስ የሚጫወቱበት ጊዜም ነበር። 1993 ወይም 94 ላይ ከጃንሜዳ ትምህርት ማዕከል ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ስናደርግ እንዳጋጣሚ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት የከተራ ዕለት የነበረ በመሆኑ ለበዓሉ  የመጣው ሰው በሙሉ በጨዋታው ተማርኮ ሲያይ የነበረበትን አጋጣሚ አልረሳውም። እንደዛ ዓይነት ቁጥር ያለው ሰው የተመለከተው ጨዋታም አላስታውስም። በጣም ጥሩ ተጫዋቼች የፈሩበት ወቅት ነበር። ያ ጊዜ አልፎ አሁን ላይ ተጫዋቾች በሙያቸው ተጠቃሚ የሆኑበት እዚህኛው ጊዜ ላይ ደርሶ ማየት እጅግ የሚያስደስት ነገር ነው።”

ያሬድ የሴቶቹን ጥሪ ተቀብሎ የያዘው የአዲስ ኮከብ ቡድን ውስጥ በትልቅ ደረጃ በመጫወት እስከ ብሔራዊ ቡድን የደረሱ እየሩሳሌም ነጋሽ  (የመጀመሪያዋ የብሔራዊ ቡድኑ አምበል)፣ ራሄል ደገፈኝ ፣ ፍሬወይኒ ሙሳ ፣ ሙና አበበ፣ ዘይነባ መሠረት መሰል ተጫዋቾችን በታዳጊነት ዘመናቸው ማሰልጠን ችሏል። በወቅቱ አዲስ ኮከብ በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአራት ቡድኖች መካከል ይደረግ በነበረው ውድድር ላይ ተካፋይ ነበር። 1993 ላይ አዲስ ኮከቦች በያሬድ ቶሌራ እየተመሩ ከአቶ ይተፋ ገብረሚካኤል ሰለሞን ኢንጅነሪንግ ፣ ከደረጄ ነጋ የካ ቅዱስ ሚካኤል ፣ ከፍቃዱ ማሞ ጃን ሜዳ ትምህርት ማዕከል ጋር በዙር በተደረገው ውድድር በየካ ቅዱስ ሚካኤል በአንድ ጎል ተበልጠው ሁለተኛ ሲወጡ በጥሎ ማለፍ ውድድሩ ደግሞ የካን በመርታት አሸናፊ መሆን ችለዋል። 1994 ላይ የብርሀኑ ግዛው ምስራቅ ሐረር ቡድን ተጨምሮ ተሳታፊዎቹ ወደ አምስት ከፍ ሲሉም የያሬድ ቶሌራው አዲስ ኮከብ ነበር ቻምፒዮን መሆን የቻለው። ያሬድ በእነዚህ ሁለት ዓመታት የአዲስ አበባን የሴቶች ምርጥ ቡድን በምክትል አሰልጣኝነት ይዞ በክልል ውድድሮች ላይም ተሳትፏል። 

በጃን ሜዳ ለብቻው የሴቶች ሜዳ ተከልሎለት ተመልካቹም በቁጥር እየጨመረ በመጣበት ወቅት የብሔራዊ ቡድኑን መመስረትም ተከትሎ የክለቦች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ሆኗል። ያሬድም 1995 ላይ በረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ ዘለቀ አማካይነት የመጀመሪያ ደረጃ የአሰልጣኝነት ሥልጠናን መውሰድ የቻለ ሲሆን እስከ 1997 ድረስ ከአዲስ ኮከብ አልተለየም ነበር። በእርግጥ 1996 ላይ ውድድሩ በአንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ቡድኖች ተከፍሎ ሲጀምር እና አዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር መመዝገቢያ ማስከፈል ሲጀምር  አዲስ ተስፋ ክፍያውን መፈፀም ተስኖት በነበረበት ጊዜ የሴቶች እግርኳስ ባለውለታው አለባቸው ተካ ደርሶለት ነበር ወደ ውድድር የገባው። በቀጣይ ዓመት ደግሞ  አዲስ ኮከብ በፋሲል ተወልደ እና ሚስተር ብራዬን አማካይነት ‘ኤግልስ’ ከተባለ በአሜሪካኖች ከሚረዳ ቡድን ጋር ተዋህዷል። ይህ በድን በፋሲል ተወልደ ሲሰለጥንም ያሬድ በአማካሪነት ሲሰራ ቆይቷል። 

በዚህ ሂደት ውስጥ በመጀመሪያው የሀገሪቷ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ምስረታ ላይ በአዲስ ተስፋ በኩል ተጫዋቾችን በማብቃት የበኩሉን የተወጣው ያሬድ ቶሌራ ጠቅልሎ ወደ ወንዶች እግርኳስ የገባበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ከሴቶቹ ጎን ለጎን 1996 ላይ የአዲስ አበባን የወንዶች የ17 ዓመት በታች ምርጥ ቡድን በምክትል አሰልጣኝነት በመያዝ ለውድድር ወደ ድሬዳው ሄዶ ሲመለስ ቡድኑን መድን ተቅልሎ ሲይዘው በዛው አብሮ ወደ መድን አምርቷል። በቀጣዮቹ ዓመታትም ከተለያዩ የሴቶች ቡድኖች ጥያቄ ቢቀርብለትም ከመድን ጋር በነበረው ውል ምክንያት በወንዶቹ እግር ኳስ ቀጥሏል። የደደቢት እና የለገጣፎ የአሰልጣኝነት ምዕራፉም ከዚሁ የቀጠለ ነበር።

ሴቶችንም ወንዶችንም በተለያዩ የዕድሜ ዕርከኖች የማሰልጠን ዕድሉ የገጠመው ያሬድ ቶሌራ ዳግም ወደ ሴቶች እግርኳስ የመመለስ ሀሳቡ እንዳለ ነው። ባገኘው አጋጣሚ የሴቶች የሊግ ውድድሮችን ለመከታተል እንደሚሞክር የሚናገረው ያሬድ በእግርኳሱ ሴቶችን ከወንዶች ጋር ሲያነፃፅር የታዘበውን ሲናገር። “የሴቶች እግርኳስ ሥልጠና ውስጥ ከተጫዋቼች ጋር በማግባባት ፣ ሀሳባቸውን በመረዳት ፣ በማስታመም በቅርበት ተግባብቶ መሥራትን ይጠይቃል። በብዙ ጫና ውስጥ ወደ እግርኳሱ ስለሚመጡ በቶሎ ተስፋ ሊቆርጡ የሚችሉበት ዕድልም የዛኑ ያህል ያሰፋ በመሆኑ በጣም ጥንቃቄ እና ትዕግስትን ይጠይቃል። በሥልጠናው ረገድ ግን ከወንዶችም የተሻለ አቀባበል ነው ያላቸው። ቁጭ ብሎ በመነጋገር ያምናሉ ፤ የመቀበል እና የመተግበር ተነሳሽነታቸውም ከፍያለ ነው።” ይላል፡፡ ለዚህም ይመስላል “አንድ ቀን ወደ ሴቶች እግርኳስ እመለሳለሁ” ሲል ወደፊት በሴቶች አሰልጣኝነቱ እንድንጠብቀው ቀጠሮ የሰጠን።

እንደሀገር የሴቶች እግርኳስ የተነቃቃበት እና ከፍ ወዳለ እርከን በተሸጋገረበት ዘመን ላይ ከወቅቱ ድንቅ ተጫዋቾች ጋር በራሱ ቡድን ውስጥም ሆነ በተቃራኒ መገናኘቱ እና ሂደቱን በቅርበት መከታተሉ ያሬድ በዘርፉ ያለው ዕድገት እንደአጀማመሩ የተፋጠነ እንዲሆን ሀሳብ ለመሰንዘር ብቁ ያደርገዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት የሰጠባቸው ሁለት ሀሳቦች ደግሞ በአመዛኙ በሙያው ውስጥ ያሉ ሰዎችን በትምህርት በማብቃት እና ለቀደምት ባለሙያዎች ተገቢውን ክብር መስጥት ላይ ያጠነጥናሉ። በሀሳቡም “አስታውሳለሁ በዚያ ወቅት የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረ ሚስተር ሀንሰን ዶረስ የተባለ ሰው በአቶ ብርሀኑ ከበደ (sport friends) አማካይነት ወጪው ተችሎ መጥቶ የሴቶች እግርኳስ ላይ ለሚሰሩ አሰልጣኞች በአዲስ አበባ ስታዲየም ሥልጠና ሰጥቶ ነበር። ሥልጠናው በሴቶች እግር ኳስ ላይ በነበሩ ደካማ ጎኖች በተለይም ረጅም ኳስ የመጣል ፣ በግንባር የመግጨት ፣ የአካል ብቃት እና ፍጥነት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ነበር። ከሥልጠናው በኋላ በራሴም ሆነ በሌሎቹ ቡድኖች ላይ ለውጥ አይቻለሁ ማለት እችላለሁ። ወደ ውጪ ወጥቶ መሠልጠን ቢቸግር እንኳን ይህ ዓይነት ልምድ ቢቀጥል መልካም ነበር። በእርግጥ አሁን ላይ እነሰላማዊት ዘርዓይ ፣ መሠረት ማኒ ፣ ህይወት ዓረፋይነ ዓይነት ኢንስትራክተሮችን ማፍራት በራሱ በሴቶች እግርኳስ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ዕድገት ነው። በዚህ መልክ አሰልጣኞችን ማብቃት ላይ በሚገባ ከተሰራ እና ለወንዶች የሚሰጠውን ትኩረት ያህል ከተሰጠው የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ይደራሳል ብዬ አምናለሁ። ሌላው በሴቶች እግርኳስ አስተዋፅኦ የነበራቸው ሰዎችን የሚገባቸውን ክብር መስጥጠት ጉዳይ ነው ፤ ፈረንጆቹ የሚበልጡንም በዚህ ነው። ለምሳሌ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በሙያው የለፉ እንደእነ አቶ ኢተፋ ገብረሚካኤል ዓይነት ሰዎች አሁን ላይ የት እንዳሉ እንኳን አይታወቅም፤ ለሰሩት ሥራ ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል። በዚህ አጋጣሚም በግሌ ለአቶ ኢተፋ ያለኝን  ክብር እና ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ። ነፍሳቸውን ይማርና አቶ ሰዒድ እንዲሁም የምስራቅ ሐረር ቡድን መሪ አቶ ቢተው ፣ የአዲስ ኮከብ ቡድን መሪ አቶ ብርሀኑ ከበደ ፣ የየካ ቅዱስ ሚካኤል ቡድን መሪ አቶ አበበ መኮንን እንዲሁም በዚያን ጊዜ የነበሩ አሰልጣኞች ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል እላለሁ።”

ከዛሬው የሴቶች ገፅ ዕንግዳችን አሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ ጋር የነበረንን ቆይታ ያጠቃለልነው በአዲስ ኮከብ እና አዲስ አበባ የሴቶች ምርጥ ቡድኖች ውስጥ ባሰለጠነባቸው ጊዜያት ውስጥ የማይረሳቸውን ሁለት አጋጣሚዎች አጫውቶን ነው። “1994 ላይ በየካ ቅዱስ ሚካኤል በአንድ ጎል ተበልጠን ዋንጫ ስናጣ ተጫዋቾች እንዴት እንዳለቀሱ እና ማባበል እንዴት እንደሚከብድ ያየሁበት መቼም የማልረሳው አጋጣሚ ነው። ሌላው የራሄል ደገፈኝን አጋጣሚ ላንሳ። በጊዜው ትልቅ ተጫዋች ሆና ለብሔራዊ ቡድን መጫወት እንደምትችል አስብ ነበር። በአዲስ አበባ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተጫዋች ሆና ናዝሬት ለውድድር የነበርንበት ጊዜ ላይ ነበር። ያው በወቅቱ ተጫዋቾች ገቢም አልነበራቸውም ፤ የራሄል ቤተሰቦችም ወደ አረብ ሀገር እንድትሄድ ይፈልጉ ነበር። ናዝሬት ላይ ከደቡብ ምርጥ ጋር ልንጫወት በነባረበት ሰዓት ላይ ከቤት ይደወልላት እና ፕሮሰሱ እንዳለቀ እና ወደ አዲስ አበባ እንድትመጣ ይነገራታል። ከዛም በለቅሶ ታጅባ የአዲስ ኮከብ መለያ ማስታወሻ ተስጥቷት ከቡድኑ ተለይታ ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ አዲስ አበባ ትመጣለች። ይሄን ጊዜ እንደአጋጣሚ ሆነና የጉዞው ሂደት ባለመጠናቀቁ በድጋሚ ወደ ናዝሬት መጥታ ቡድኑን ተቀላቀለች። ያ ጊዜ እና ጉዞውም አልፎ እርሷም እንደተጫዋች አድጋ ብሔራዊ ቡድኑን በአምበልነት እስከመምራት ደርሳ ከዛ በኋላ ደግሞ በዲቪ ወደ አሜሪካ የሄደችበትን የህይወት ገጠመኟን አልረሳውም።”

© ሶከር ኢትዮጵያ