የጣና ሞገዶቹ አጥቂ አስፈርመዋል

ለመቐለ 70 እንደርታ ለመጫወት ፊርማውን አኑሮ የነበረው የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ አዲስ በወጣው የዝውውር ደንብ መሠረት ባህር ዳር ከተማን ተቀላቅሏል።

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት ባህር ዳር ከተማዎች የበርካታ ነባር ተጫዋቾቻቸውን ውል ካደሱ በኋላ በክፍተቶቻቸው አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው መቀላቀላቸው ይታወሳል። ከወር በፊትም መቀመጫቸውን በክልላቸው ባህር ዳር በማድረግም የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሲያከናውኑ ሰንብተዋል።

ከነገ በስቲያ ለሚጀምረው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመሳተፍ ከስድስት ቀናት በፊት አዲስ አበባ የመጡት ሞገዶቹ ከደቂቃዎች በፊት ምንይሉ ወንድሙን የግላቸው ማድረጋቸው ተረጋግጧል። ከ2006 ጀምሮ በመከላከያ ቆይታ የነበረው እና በቆየባቸው ዓመታት በርካታ ጎሎችን ያስቆጠረው ምንይሉ ከሁለት ወራት በፊት ለመቐለ 70 እንደርታ ለመጫወት ወስኖ ነበር። ይሁን እና በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ምክንይት ሦስቱ የክልሉ ክለቦች በሊጉ የሚሳተፉበት እድል መጥበቡን ተከትሎ በክለቦቹ የሚገኙ ተጫዋቾች በልዩ መልኩ በተዘጋጀ የዝውውር ደንብ ለዘንድሮ ብቻ ወደ ሌላ ክለብ ሄደው እንዲጫወቱ መወሰኑን ይታወቃል። ይህንን ታሳቢ በማድረግም ምንይሉ ወንድሙ ከደቂቃዎች በፊት በዘንድሮ የውድድር ዓመት ውሀ ሰማያዊውን መለያ ለማጥለቅ ፊርማውን በፌዴሬሽን ተገኝቶ አኑሯል።

ከዚህ ቀደም ባህር ዳር ከተማዎች መናፍ አወልን፣ በረከት ጥጋቡ፣ አህመድ ረሺድ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና አፈወርቅ ኃይሉን ለሁለት ዓመት ማስፈረማቸው ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ