የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 1-4 አዳማ ከተማ

በአዳማ ከተማ 4-1 አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የሊጉ አንደኛ ሳምንት አራተኛ ጨዋታ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ለሱፐር ስፖርት እንዲህ አጋርተዋል።
አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው…

“ተጫዋቾቼን ተወቃሽ አላደርግም። ሰባተኛው ደቂቃ ላይ አንድ ለናቱ የነበረን በረኛ በቀይ ወጥቷል። እንደውም የሜዳ ላይ ተጫዋች ነው ያስገባሁት። እኔ አልተከፋሁም ደስተኛ ነኝ።”

ቡድኑ ሙሉ ስብስቡን መጠቀም ስላለመቻሉ እና ቀጣይ ዕጣ ፈንታው…

“እነዚህ ተጫዋቾች ያልቅላቸዋል አያልቅላቸውም የሚለው የእኔ የቤት ሥራ አይደለም። ዛሬ የተመለከታችኋቸው ተጫዋቾች ወጣቶች ናቸው። ተጠባባቂ ላይ ያሉት ዘጠኝ ተጫዋቾችም ከጨዋታ ውጪ ናቸው። ጥሩ ዝግጅትም አላደረግንም ፤ የቀን እጥረትም ነበር። ፈታኝ ነው ፤ ሰቆቃ ላይ ነው ያለነው። እኔ ውጤቱ ቅር አላሰኘኝም። ወደፊት ግን የሚፈጠረው ነገር ምን ይሆናል የሚለውን ከዚሁ ለመተንበይ ከባድ ነው። ተጫዋቾቹ ካለቀላቸው እና ተሟልተን ከገባን ሁለት በረኞች አሉን በተዘጋጀንበት አጭር ጊዜ የአቅማችንን ለመስራት እንታገላለን።”

አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

ስለ ግብጠባቂው በቀይ መውጣት እና ስለፈጠረው ተፅዕኖ…

“ሜዳ ላይ የነበረውን እንቅስቃሴ ከተመለከትን በኃላ እንደሞናሸንፍ ዕምነቱ ነበረኝ ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የበረኛው መውጣት ተፅዕኖ አለው ያም ቢሆን ግን ተፅዕኖ ፈጥረን መጫወት ችለናል።”

በሁለተኛው አጋማሽ አጥቂ ጨምረው ስለመጫወታቸው እና ከጨዋታው ስላገኙት ትምህርት…

“የዝግጅታችን ጊዜ በጣም አጭር ነበር ፤ የኮቪድ ምርመራ ጨምሮ አዲስ ቡድን እንደመገንባታችን አስቸጋሪ ነበር። ነገር ግን እንደተመለከታችሁት ያመጣናቸው በተለይ በሁለተኛ አጋማሽ ያስገባናቸው ተጫዋቾች ወጣቶች እና ከታችኛው ሊግ ያመጣናቸው ቢሆንም በራስ መተማመን ያላቸው ናቸው።”

ግብ ስላስቆጠሩት ተጫዋቾች…

“አብዲሳ ጉዳት ላይ የነበረ ተጫዋች ነው ፤ በዝግጅት ወቅት ጉዳት አስተናግዶ በማገገም ላይ የነበረ ተጫዋች በመሆኑ ነው ቀይረን ያስገባነው። ጥሩ አቅም ያለው ተጫዋች ነው ወደፊትም ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም ማበርከት የሚችል ልጅ ነው። ታፈሰ ደግሞ በራስ መተማን ሰጥተነው ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል።”

የዛሬው ጨዋታ ውጤት በቀጣይ ስለሚኖረው ጥቅም…

” ለቀጣይ ትልቅ ተነሳሽነት ይፈጥርልናል ፤ በቀጣይ ላሉብን ጨዋታዎች ከፈጣሪ ጋር ጠንክረን እንቀርባለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ