የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዛሬ ውሎ አስገራሚ ክስተት…

“ከዚህ ያነሰ ጎል ባስተናግድ ደስ ይለኝ ነበር” – ኢደል አሚን ናስር

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ከሰዓት ላይ በተደረገ ጨዋታ አዳማ አባ ጅፋርን 4-1 በረታበት ጨዋታ ላይ አስገራሚ ክስተት ተፈጥሯል።

በፊፋ በተጣለበት እግድ ምክንያት ቡድኑን በ2013 የውድድር ዘመን ያጠናክራሉ ተብለው የታሰቡ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማፀደቅ ያልቻለው ጅማ አባጅፋር አንድ-ለናቱ የነበረውን ግብጠባቂ አቡበከር ኑሪ ገና በስምንተኛው ደቂቃ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ምንም አይነት ተቀያሪ ግብጠባቂ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ያልነበራቸው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው(ማንጎ) የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ኢደል አሚን ናስር ባስገዳጅ ሁኔታ ለማስገባት መገደዳቸው አስገራሚ ክስተት ሆኖ አልፏል። ይህን ተከትሎ የተፈጠረውን አጋጣሚ አስመልክቶ ባልተለመደ ሁኔታ ግብጠባቂ ሆኖ ለመጫወት የተገደደው ኢደል አሚን ናስርን አስርተነዋል።

ትውልድ እና የእግርኳስ ተጫዋችነት ጅማሮ…

የተወለድኩት ጅማ ከተማ ነው። በአሰልጣኝ ጋሻው መኮንን ፕሮጀክት ስሰለጥን ቆይቻለሁ። ይህ ፕሮጀክት እነ ሳላዲን ሰዒድን ያፈራ ፕሮጀክት ነበር። ከዚህ በመቀጠል ወደ አምቦ አካዳሚ በመግባት የግራ መስመር ተከላካይ እና የአማካይ ተከላካይ በመሆን ለአምስት ዓመት በመጫወት ቆይቼ ዘንድሮ ነው ጅማ አባጅፋርን መቀላቀል የቻልኩት።

ከዚህ ቀደም ግብጠባቂ ነበርክ ?

ኧረ በፍፁም ሆኜ አላውቅም። አንዳንዴ በሠፈር ውስጥ ሰው ሲጎል እና በቁጥር ተጠርቶ ተቀያይረን እገባለው እንጂ ግብጠባቂ ሆኜ አላውቅም፤ የመሆን ሀሳቡም ፍላጎትም የለኝም። የእድሜዬን አብዛኛውን ጊዜ በእግርኳስ ተጫዋችነት ነው ያሳለፍኩት።

ታዲያ ተነስተህ ግባ ስትባል ምን ተሰማህ?

በጣም ደንግጫለሁ። ግን ያለው አማራጭ ቁመት ያለኝ እኔ ነኝ፣ ትንሽም ደፈርኩ መሰለኝ ያው ልገባ ችዬ የምችለውን ጥረት አድርጌያለሁ። ትንሽም በጨዋታው ጉዳት አጋጥሞኝ እያነከስኩ ነበር መጫወት የቻልኩት። አዲስ የፈረሙ ተጫዋቾች እና ትክክለኛ ግብጠባቂዎች ቢኖሩ ኖሮ የዛሬውን ጨዋታ በሚገባ አሸንፈን እንወጣ ነበር። ያው ዕድል አልሆነልንም፤ ኳስ አንዳንዴ እንደዚህ ነው።

አራት ጎል አስተናግደሀል፤ መታሰቢያነቱ ?

(በጣም እየሳቀ..) ከዚህ ያነሰ ጎል ባስተናግድ ደስ ይለኝ ነበር። ግን ከፈጣሪ ጋር የምችለውን አድርጌ አለው። ከዚህ በላይ ምን እላለው።

ከዚህ በኃላ ቋሚ ግብጠባቂ ትሆናለህ ?

ኧረ በፍፁም! የሚታሰብ አይደለም። ዛሬ የገባሁት ይሄን ያህል ጎበዝ ሆኜ አይደለም። ዋናው ግብጠባቂ ባለመኖሩ ክፍተቱን ለመሸፈን ነው የገባሁት እንጂ የተጫዋችነት ሚናዬን በመቀየር ግብጠባቂ አልሆንም።

በቀጣይ ካለው ክፍተት አንፃር ቋሚ ሆነህ እንድትገባ ብትደረግስ ?

ያው አሰልጣኙ ካሰለፈኝ ግዴታዬ ነው። የትም ቦታ ያድርገኝ እጫወታለው። የተሰጠኝን ኃላፊነት መወጣት አለብኝ። እስከዛ ግን የቡድናችን ችግር ይቀረፋል ብዬ ተስፋ አደርጋለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ