ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

የአንደኛው ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር የሆነውን ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።

የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ሳምንት ላይ ከተቀመጡ ጠንካራ ጨዋታዎች መካከል የሄኛው አንዱ ነው። በጥቅምት መጀመሪያ አካባቢ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት የገቡት የጣና ሞገዶቹ ዘንድሮ ከአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር የሚቀጥሉ ይሆናል። አፈወርቅ ኃይሉ፣ አህመድ ረሺድ፣ ባዬ ገዛኸኝ፣ በረከት ጥጋቡ እና መናፍ ዐወል አዳዲሶቹ የባህርዳር ከተማ ተጫዋቾች ናቸው። ባህር ዳር ዐምና ከማጥቃት ጥንካሬው በተቃራኒው የመከላከል ድክመት ነበረበት። ቡድኑ ከሲሶኮ ጋር ተለያይቶ መናፍን ከማስፈረሙ እና አህመድ ረሺድን ከማከሉ ውጪ የጎላ ለውጥ አለማድረጉን ተከትሎ አሰልጣኝ ፋሲል በምን መልኩ የኋላ ክፍሉን ያሻሽሉታል የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ውጪ ባህር ዳር የጎላ የስብስብ ለውጥ አለማድረጉ እና የቡድን ጥራት የሚጨምሩ ተጫዋቾች ማዘዋወሩ ረጅም ርቀት ከሚጓዙ ቡድኖች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ነው።

የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እና ረዳቶቻቸውን ውል በማራዘም እንዲሁም ማማዱ ሲዲቤ ፣ ያስር ሙገርዋ ፣ ተመስገን በጅሮንድ እና ጫላ ተሺታን በማስፈረም የእብዛኞቹን ነባር ተጫዋቾቹን ውል ያራዘመው ሲዳማ ከአምስት ዓመታት በኋላ ያለ አዲስ ግደህ ወደ ውድድር ይገባል። ሲዳማ ቡናን ያለ አዲስ ግደይ ማሰብ ለብዙዎች ከባድ ነው። ክለቡ ያለ ወሳኝ ተጫዋቹ በሚጀምረው የውድድር ዘመን ጫላ ተሺታ የአዲስ ቀጥተኛ ተተኪ እንደሚሆን ሲጠበቅ በየጊዜው እየጎመራ የመጣው ሀብታሙ ገዛኸኝ ይበልጥ የሚጎላበት ዕድልንም አግኝቷል። ክለቡ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የሚታወቅ ቡድን እንደመሆኑ ዝውውሮቹ ይህን ጠንካራ ጎኑን ለማጎልበት የሚረዱ እንደሚሆኑ ይገመታል። ሆኖም ለዋንጫ ለመፎካከር አፈግፍገው ከሚጫወቱ ቡድኖች ጋር በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ያላቸውን የማስከፈት ድክመት ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።

ነገ 09፡00 ላይ በሚደረገው በዚህ ጨዋታ ላይ በባህር ዳር ከተማ በኩል አፈወርቅ ኃይሉ በጉዳት የማይሰለፍ ሲሆን በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ መሳይ አያኖ እና ዮሴፍ ዮሐንስ በግል ጉዳይ እንደማይኖሩ ታውቋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ በ2011 የውድድር ዓመት በመጀመርያ ግንኙነት ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሀዋሳ ላይ አንድ አቻ ሲለያዩ ባህር ዳር ላይ ባህር ዳር ከተማ 1-0 አሸንፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ