ለሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች የእርስ በእርስ መቀራረብን ለመፍጠር የሚረዳ ስልጠና ተሰጠ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሰልጣኝ ለሆኑ ዋና እና ረዳት አሰልጣኞች የእርስ በእርስ የውይይት መድረክ እና የመማማሪያ ስልጠና ዛሬ ምሽት ተሰጥቷል፡፡

በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ላይ ላሉ ዋና እንዲሁም ረዳት አሰልጣኞች ስለ እግር ኳሱ አንድ ሀሳብ ይዘው ለእድገት እንዲሰሩ የሚረዳ የእርስ በእርስ የመቀራረቢያ እና የመማማሪያ የውይይት እና የስልጠና መድረክ ዛሬ አመሻሽ በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ተሰጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተር በመሆን በቅርቡ ተሹሞ እየሰራ የሚገኘው ቴዎድሮስ ፍራንኮ በዋናነት ይህን ውይይት በማዘጋጀት ለአሰልጣኞቹ እንዲሰጥ በማድረጉ ቅድሚያውን ቦታ የሚይዝ ሲሆን “አሰልጣኞች እርስ በእርስ እንዴት መግባባት ይችላሉ? ጥሩ እና ስነ ምግባር ያለው አሰልጣኝ ምን አይነት ነው ? መጥፎ አሰልጣኝ የምንለውስ መገለጫው ምን አይነት ነው ?” የሚሉት የምሽቱ የመወያያ ሀሳብ ነበሩ። በዚህ ላይ አሰልጣኞች በቴክኒክ ዳይሬክተሩ የቀረበው የውይይት ሀሳብ ላይ አንድ ለአምስት ሆነው ከተነጋገሩ በኃላ በስተመጨረሻ የተወያዩበትን ሀሳብ ለሰልጣኞቹ በማቅረብ አስረድተዋል። ተሳታፊ የሆኑ አሰልጣኞችም ስልጠናው መዘጋጀቱ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል። እርስ በእርስ በመተባበር የሴቶች እግር ኳስን ለማሳደግ በጋራ መስራት ይገባናል በማለት ሀሳባቸውን ገልፀዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ