ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ባህር ዳር ከተማ

በሁለተኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ሁለት ሊጉን በድል የጀመሩ ቡድኖች እርስ በእርስ የሚገናኙበት ይህ ጨዋታ ጠንካራራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ የሚጠበቅ መርሐ ግብር ነው።

በወላይታ ድቻው ጨዋታ ደካማ አጀማመር አድርጎ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና በሂደት ወደ ጨዋታው ለመመለስ እና አሸናፊ ለመሆን ችሏል። ይህንን ለማድረግ ግን የዳዋ ሆቴሳ ልዩ ብቃት አስፈልጎት ነበር። የቡድኑ የአማካይ ክፍል ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች መገንባቱ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ምት መግባት እንዲችል ቢያደርገውም ደካማ አጀማመር እንደነገው ዓይነት ባሉ ጨዋታዎች ላይ ሊፈትነው እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። የድቻው ድል ከዳዋ የግል ብቃት በላይ የቡድን ስራው ጥንካሬ ያመጣው እንደሆነ ለማረጋገጥም የነገው ጨዋታ ክብደት መለኪያ ሊሆን ይችላል። ቡድኑ ከግራ መስመሩ ከሚነሳው የማጥቃት ጥንካሬው ባለፈ የሱለይማን ሀሚድን አደገኛ ተሻጋሪ ኳሶች ጥራት ማግኘት ከቻለ በነገው ጫና የተሻለ ስለት ሊኖረው ይችላል። ዳዋ ከመስመር ወደ መሀል ወደ ሳጥኑ መግቢያ ላይ በመግባት የሚያደርገው እብቅስቃሴ የሚፈጥራቸው ክፍተቶች የባህር ዳርን የተረጋጋ የተከላካይ አማካዮች ጥምረት ጋር የሚኖረው ፍልሚያ በጨዋታው ከሚጠበቁ ፍልሚያዎች መካከል አንዱ ይሆናል።

ባህር ዳር ከተማ ሲዳማ ቡናን በረታበት ጨዋታ በርካታ ጥንካሬዎች ታይተውበታል። እነዚህ ጥንካሬዎች በተከታታይ ጨዋታዎች መደገም ከቻሉ ቡድኑ በውድድር ዓመቱ የሚኖረውን ጉዞ ቀጣይነት የሚያሳይ ይሆናል። የቡድኑን የማጥቃት ሂደት አስፈሪ ያደረገው የፍፁም ዓለሙ እና ባዬ ገዛኸኝ ድንቅ አቋም ላይ መሆን እሴንዴ አይዛክ እና ቴዎድሮስ በቀለን ጥምረት በሚጋፈጥበት የነገው ጨዋታ የባህር ዳር የመስመር ተከላካዮች ከቀደመው ጨዋታም የተሻለ የማጥቃት ተሳትፎ በማድረግ የማጥቃት ሚናቸው ከፍ ሊል እንደሚችል ይጠበቃል። ከዚህ ጎን ለጎን ግን የዳዋን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ከኋላ ክፍሉ የሚጠበቅ ይሆናል። በአመዛኙ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት የሚሞክሩት ባህር ዳሮች የተሻለ ልምድ ካለው የሀዲያ ሄሳዕና የአማካይ ክፍል ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያም የሚፈጥሯቸውን የጎል ዕድሎች ጥራት መወሰኑ የማይቀር ነው። በዚህ ረገድ ቡድኑ ሊጉን ከጀመረበት ጨዋታ አንፃር እንደ ሄኖክ አወቀ ላሉ በመጀመሪያው ጨዋታ መልካም ተሰጥኦዋቸውን ላሳዩ አማካዮች የሚሰጠው ደቂቃ ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች የነገውን ከባድ ፍልሚያ ያለጉዳት እና ቅጣት በሙሉ ስብስባቸው እየተጠባባቁ ሲሆን በባህር ዳር በኩል ግን አፈወርቅ ኃይሉ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆን በሲዳማው ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው የቁልፍ ተጫዋቻቸው ፍፁም ዓለሙ የመሰለፍ አለመሰለፍ ጉዳይ ነገ እንደሚወሰን ሰምተናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሀዲያ ሆሳዕና 2008 ላይ ወደ ሊጉ መጥቶ በዛው ዓመት ሲወርድ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ 2011 ላይ ነበር ያደገው። በዚህም በተሰረዘው የውድድር ዓመት ተገነኝተው 2-2 ከተለያዩበት ጨዋታ ውጪ ነገ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

መሐመድ ሙንታሪ

ሱሌይማን ሀሚድ – ኢሴንዴ አይዛክ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

አዲስ ህንፃ – አማኑኤል ጎበና – መድሃኔ ብርሀኔ

ዱላ ሙላቱ – ቢስማርክ አፒያ – ዳዋ ሆቴሳ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ሀሪስተን ሄሱ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ሳምሶን ጥላሁን

ወሰኑ ዓሊ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ

ባዬ ገዛኸኝ


© ሶከር ኢትዮጵያ