አንዳንድ ታክቲካዊ ነጥቦች በሁለተኛው ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዙርያ…

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንት ተከናውነው ሲጠናቀቁ ከታዘብናቸው ታክቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

በቁጥር መበለጥ ያላቆመው ኢትዮጵያ ቡና…

በሳምንቱ ከተደረጉ ትኩረት ሳቢ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የፋሲል ከነማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ነበር። በጨዋታው ተመስገን ካስትሮን በቀይ ያጣው ኢትዮጵያ ቡና የተፈጠረበትን የቁጥር ብልጫ በመቋቃም ተጨማሪ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ጨዋታውን ማሸነፍ ችሏል። ይህን ከባድ ፈተና እንደ ፋሲል ባለ ጠንካራ ተጋጣሚ ላይ መወጣት አዳጋች እንደሆነ እሙን ነው። ያም ስለሆነ ነው ሶከር ኢትዮጵያ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ ስትል የሰየመችው። በአሰልጣኙ ውሳኔ በመታገዝ ኢትዮጵያ ቡና የተጋጣሚውን የመሀል ሜዳ የቁጥር ብልጫ ለመቋቋም እና በመልሶ ማጥቃት ስል ሆኖ ለመገኘት ስለቻለበት መንገድ ደግሞ ጥቂት እንበል።

የመሐል ተከላካዩ ተመስገን ካስትሮ በቀይ ከወጣ በኋላ አሰልጣኙ አማካያቸው ዓለምአንተ ካሳን በተከላካዩ ምንተስኖት ከበደ ነበር የተኩት። በመሆኑም ቡድኑ ከኃላ የተሟሉ አራት ተከላካዮች ኖሩት። አማኑኤል ዮሃንስ እና ታፈሰ ሰለሞን አማካይ ቦታ ላይ የፋሲሉን የመሀል ክፍል የመጋፈጥ ኃላፊነትም ወደቀባቸው። በዚህ ወቅት ነበር ፋሲል መሀል ሜዳ ላይ በአማካዮቹ ኳስን በቅብብል በመያዝ ቀዳዳዎችን ለመፈለግ ሲጥር ከቡና የመስመር ተከላካዮች ለእንቅስቃሴው የቀረበው አንዱ (ኃይሌ ገብረትንሳይ ወይም አስራት ቱንጆ) አማካይ ክፍል ላይ የሚኖረውን የቁጥር ብልጫ ለማካካስ ወደ መሀል የሚገቡት። ይህን እንቅስቃሴ እንደ ሀሰተኛ የመስመር ተከላካይ (false full back) በመሆን ለመከወን ሲሞክሩ የእነርሱ ቦታ ደግሞ በቀኝ በአቡበከር ናስራ በግራ ደግሞ በዊልያም ሰለሞን ይሸፈን ነበር። ይህን እንቅስቃሴ በፍጥነት መከወናቸው መሀል ሜዳ ላይ የተጋጣሚያቸው ቅብብል የሚፈልገውን ክፍተት በቶሎ ለመዝጋት እና ለማጨናገፍ ሲረዳ ዕቅዱ በመስመር የሚፈጠረውም ሌላ ክፍተት ስለተሸፈነ ተጨማሪ ቀዳዳ እንዳይፈጠር ዕድል ይሰጣል። ከዚህም ባለፈ ቡድኑ ኳስ ሲነጠቅ ፊት ላይ ተነጥሎ የሚቆየው አጥቂ ሀብታሙ ታደሰ ኳሶችን የመቀበል ዕድል ሲኖረው ቡድኑ ወደ ማጥቃት ሲሸጋገርም የመስመር ተከላካዮቹን ሚና የተኩት መስመር አጥቂዎች የጥቃቱ አካል ይሆናሉ።

መሰል የሜዳ ላይ ሚና ሽግሽጎች የጎደለውን ተጫዋች የስራ ድርሻ በቡድን ስራ የመሸፈን አቅምን ሲፈጥሩ ተጋጣሚ ሁኔታውን ካልተረዳ እና ምላሽን ካልሰጠ ደግሞ ሌላ ዓይነት የማጥቃት በረከትንም ይዘው ይመጣሉ። የዚህ ተጠቃሚ የነበረው ቡና ጨዋታውን ማሸነፉ ብቻ ሳይሆን ለድንገተኛ ችግር የተዋጣለት መፍትሄ ማዘጋጀቱ ትልቅ ጥንካሬው ሆኖ ታይቷል።

እርጋታን የተላበሰው ወላይታ ድቻ …

በሁለተኛው ሳምንት እጅግ ተሻሽለው ከመጡ ቡድኖች መካከል ዋነኛው ወላይታ ድቻ ነው። በመጀመሪያው ጨዋታ ጥሩ አጀማመር በማድረግ ሀዲያ ሆሳዕናን መምራት ችሎ የነበረው ቡድኑ ቀስ በቀስ የእንቅስቃሴ የበላይነቱን አሳልፎ በመስጠት ለሽንፈት ሲዳረግ ተመልክተነዋል። አዳማ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ ግን የአሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ቡድን የታየበትን ግልፅ ድክመት በማረም የተዋጣለት 90 ደቂቃ አሳልፏል። ይህንን ለማድረግ የረዳውን የአማካይ ክፍሉ በሽግግሮች ወቅት የነበረውን በትጋት የታጀበ እንቅስቃሴ ለመመልከት እንሞክራለን።

በአሰላለፍ ደረጃ ለ 4-1-4-1 የቀረበ አደራደር ይዞ የገባው ድቻ አጣማሪው የነበረው አብነት ደምሴን በማሳረፍ በረከት ወልዴን በብቸኛ ተከላካይ አማካይነት ተጠቅሟል። ከእርሱ ፊት ኤልያስ አህመድ እና እንድሪስ ሰዒድ ሲጣመሩ በሁለቱ መስመሮች ደግሞ ፀጋዬ ብርሀኑ እና ቸርነት ጉግሳ ከፊት አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱ ጀርባ በሜዳው ጎን የአራት ተጫዋቾች መስመር ሰርተው ተሰልፈዋል። የኳስ ቁጥጥርን የሚያዘወትረው የአዳማ አማካይ ክፍል ምስረታውን ሲጀምር ፊት ላይ ጫና መፍጠር ከሚጀምረው ስንታየሁ ጀርባ ያሉት አማካዮች ከበረከት ጋር ያላቸው ክፍተት በመቀነስ የቅብብል ክፍተቶችን ይዘጋሉ። በመሆኑም የአዳማ ጥቃት ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ከመድረሱ በፊት ለማፈን እና በቶሎ ወደ ማጥቃት ሽግግር ውስጥ ለመግባት ድቻዎች አካላዊ እና አዕምሯዊ ዝግጅት ኖሯቸው ታይተዋል። በተለየም ሁለተኛው ጎል የተቆጠረበት መንገድ ይህንን በግልፅ የሚያሳይ ነበር።

ከዚህ ባለፈ ድቻዎች ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር የአማካይ መስመሩ ያለቅጥ ወደራሱ ሜዳ ቀርቦ ለመልሶ ማጥቃቱ እንዲርቅ እና ራሱን እንደመጀመሪያው ጨዋታ ጫና ውስጥ ለመክተት ምልክት የሰጠበትን ሁኔታ በቶሎ አሻሽለዋል። የመጀመሪያውን አካሄዳቸውን ዳግም ስራ ላይ በማዋል ግን ደግሞ ኳስ ካስጣሉ በኃላ በፍጥነት ወደ ፊት ከመሄድ ይልቅ ኳሱን በተቻለ መጠን ለመያዝ ያረጉት ጥረት የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት ሞራል ቀስ በቀስ አውርዶታል። በተለይም ወደ ጨዋታው ማብቂያ ላይ በራሳቸው የግብ ክልል ጭምር ጫና ውስጥ ሆነው እንኳን ቅብብሎችን ተረጋግተው በመከወን ከተጋጣሚ የጫና አጥር ይወጡ የነበረበት መንገድ አድናቆትን የሚያስችር ነበር።

የቁልፍ አማካዮችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር…

አማካይ ክፍል ላይ የሚሰለፉ የቡድኑን የኳስ ፍሰት የሚያሳልጡ ፣ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥሩ እና ግብም የሚያስቆጥሩ ተጫዋቾች በቀላሉ የዓይን ማረፊያ ይሆናሉ። ታድያ ተጋጣሚዎች እነዚህ ተጫዋቾችን የማቆም ዕቅድ ይዘው ሲገቡ ቡድኑ እነሱን በእንቅስቃሴ ነፃ የሚያስወጣ ሌላ ሀሳብ ይዞ ወደ ሜዳ ካልገባ የኳስ ስርጭቱ በቀላሉ የመቋረጥ ችግር ይገጥመዋል። የባህር ዳር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ለዚህ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።

በሦስት የመሀል ተከላካዮች እና ከኳስ ውጪ የተከላካይ መስመሩን ቁጥር ወደ አምስት ከፍ በሚያደርጉ የመስመር ተመላላሾች (Wing backs) ጨዋታውን የጀመረው የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለው ሀዲያ ሆሳዕና ለጣና ሞገዶቹ በሚፈልጉት መጠን ወደ ሳጥን የመድረስ ዕድል አልሰጣቸውም። በጨዋታው ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ የመጣው ተከላካይ አማካዩ ተስፋዬ አለባቸውም የባህር ዳሩን ፍፁም ዓለሙ እንቅስቃሴ የማምከን ዋና ተግባር ሲፈፅም ተስተውሏል። ኃይልን የቀላቀለው የቡድኑ የመከላከል አጥር በማጥቃት ላይ ወደ ፊት ሲሄድ አቅም እንዲያንሰው ምክንያት ይሁን እንጂ የተጋጣሚውን የማጥቃት ጉልበት በማምከኑ ግን ተዋጥቶለታል። በቅብብሎቹ ከተከላካይ ጀርባ መግባት የከበደው የባህር ዳር ቡድን የወገብ በላይ ስብስብ ተደጋጋሚ ጉሽሚያዎችን ማስተናገዱ በነበረበት የማጥቃት መንፈስ ላይ እንዳይቆይ ጉልህ ድርሻ ነበረው። በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ልዩነት መፍጠር የሚችለው ፍፁም ደግሞ የዚህ ዕቅድ ዋነኛ ሰለባ ሆኖ ነበር።

በዚህ አኳኋን ተጋጣሚውን ማዳከም የቻለው ሀዲያ ሆሳዕና በሁለተኛው አጋማሽ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቹን ወደ አራት ቢቀንስም ለባህር ዳር በተሟላ አደረጃጀት ወደ መጀመሪያው የማጥቃት ሞራል መመለስ ቀላል አልሆነለትም። ይህንን ተቋቁሞ ግብ ለማግኘት ያደርግ የነበረው ተደጋጋሚ ሙከራ እስከመጨረሻው መቀጠሉም በፈጣን ሽግግር በተገኘ ረጅም ኳስ ግብ ለማስተናገድ ዳርጎታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደ ሀዲያ ሆሳዕና የጎላ የኃይል አጠቃቀም ባይታከልበትም የድሬዳዋው ኤልያስ ማሞ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ሙሉዓለም መስፍን ዕይታ ውስጥ መቆየቱ የወትሮውን የፈጣሪ አማካይነት ሚና እንዳይወጣ ሲያስተጓጉለው ተስተውሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ