ወልቂጤ ከተማ ፎርፌ ይገባኛል አለ

ወልቂጤ ከተማ በሁለተኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባደረገው ጨዋታ ዙሪያ ክስ አቅርቧል።

በሁለተኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ያለግብ መለያየታቸው ይታወሳል። በጨዋታውም ጅማ አባ ጅፋር በአዲስ መልክ ያሰፈረማቸውን እና በመጀመሪያው ጨዋታ ያልተጠቀመባቸውን ተጫዋቾች አሰልፎ አጫውቷል። ይህንን ጉዳይ መነሻ በማድረግም ነው ወልቂጤ ከተማ ከትናንት በስትያ የተጨዋች ተገቢነት ክስ በጅማ ላይ ያነሳው።

ክለቡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው እና ለሊጉ አክሲዮን ማህበር ግልባጭ ባደረገው ደብዳቤ ጅማ አባ ጅፋር እንደ ትርታዬ ደመቀ እና ጃኮ ፔንዜ ዓይነት ተጫዋቾችን መጠቀሙን ጠቅሶ በፎርፌ የጨዋታው አሸናፊ በመሆን ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል እንደሚገባው ገልጿል። ክለቡ የተገቢነት ክሱን ያነሳበት ምክንያት ጅማ አባ ጅፋር የተጫዋቾች ደመወዝ ባለመክፈሉ በፊፋ በተጣለበት እገዳ ምክንያት ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች መጠቀም በማይችልበት ሁኔታ በማሰለፉ ነው ብሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ