“ምንም ቢሆን የራሴን ነገር አላስቀድምም” – አቤል ያለው

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጋቸው የዘንድሮ ዓመት ጨዋታዎች ሁሉ የእርሱ ሚና ከፍተኛ እየሆነ ከመጣው አቤል ያለው ጋር ደምቆ ከዋለበት የዛሬው ጨዋታ በኋላ ቆይታ አድርገናል።

ሦስተኛ ሳምንት ባስቆጠረው የዘንድሮ ዓመት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ እጅግ የተሳካ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ፈጣኑ አጥቂ አቤል ያለው ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ድሬደዋን በረቱበት ጨዋታ ውስጥ ጉልህ ሚና ሲኖረው አንድ ግብን በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ሌላ ተጨማሪ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሎ እንደነበረ ይታወቃል። በዛሬውም ዕለት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ ከነማን ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር በሰፊ የጎል ልዩነት በረታበት ጨዋታ በተቆጠሩት አራት ጎሎች ሁሉ የእርሱ ድርሻ ከፍተኛ ነበር። ወቅታዊ አቋሙ ጥሩ ከሆነው አቤል ያለው ጋር ከዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ አግኝተን አዋርተናው ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቶናል።

” ለጎል የሚሆኑ ኳሶችንም አመቻችቶ በማቀበል ጎልም በማስቆጠር በሁለቱም ተግባራት አለሁ። ወደፊትም ሜዳ ላይ ስገባ ቡድኔን ለመጥቀም እስከሆነ ድረስ ካገኘሁ አገባለው ካልተገኘ ሌላው የቡድን አጋሬ ለማቀበል እሞክራለሁ። አሁን የማስቀድመው ክለቤን ብቻ ነው። ሁሌም ቢሆን ጊዮርጊስ ቤት የተሻለ ነገር ካላሳየህ ክለቡን አትመጥንም። ስለዚህ በየዓመቱ ራስህን እያበቃህ እያሻሻልክ ከፈጣሪ ጋር መምጣት አለብህ። እኔም በዛ መልኩ ዘንድሮ የተሻለ ነገር በማድረግ ራሴን አዘጋጅቼ የመጣሁት። ምንም ቢሆን የራሴን ነገር አላስቀድምም። ዘንድሮ ሻምፒዮን ለመሆን ስለምንጫወት ሁላችንም የግል ነገራችንን ትተን ክለባችን ያሰበውን ዋንጫ ለማሳካት እንጥራለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ