ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ የዓመቱ መጀመሪያ ድሉን አግኝቷል

በሦስተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የመጨረሻ ጨዋታ ወልቂጤ በያሬድ ታደሰ ብቃት የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥቡን ወላይታ ድቻ ላይ አግኝቷል።

በ2ኛ ሳምንት አዳማ ከተማን የረቱት ወላይታ ድቻዎች በእለቱ ከተጠቀሙት ስብስብ ውስጥ አንድ ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም በቅጣት በዛሬው ጨዋታ ባልተሰለፈው አናጋው ባደግ ምትክ ፀጋዬ አበራን አስገብተዋል። በአንፃሩ ከጅማ አባጅፋር ጋር ያለ ግብ በተለያዩት ወልቂጤ ከተማዎች በኩል ደግሞ አምስት ለውጦች ሲደረጉ በዚህም አሚኑ ነስሩ፣ ሥዩም ተስፋዬ፣ ሙሀጅር መኪ፣ አህመድ ሁሴን እና አሜ መሐመድን አስወጥተው በምትካቸው ቶማስ ስምረቱ፣ ተስፋዬ ነጋሽ፣ በኃይሉ ተሻገር፣ ያሬድ ታደሰ እና አብዱራህማን ሙባረክን በመጀመሪያ አሰላለፍ በማካተት ጀምረዋል።

እጅግ አሰልቺ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች በኩል እጅግ የወረደ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። ነገርግን ደካማ በነበረው አጋማሽ በ37ኛው ደቂቃ በዛሬው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታውን የጀመረው አብዱልራህማን ሙባረክ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ያሬድ ታደሰ በቀጥታ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ባስቆጠራት ግብ የመጀመሪያው አጋማሽ በሠራተኞቹ መሪነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለት መልኮች የነበሩት ነበር። በአገማሹ የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ወልቂጤ ከተማዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ በቀሪዎቹ 25 ደቂቃዎች ደግሞ ድቻዎች የተሻሉ ነበሩ።

በ46ኛው ደቂቃ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ወልቂጤ ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ረመዳን በቀጥታ መትቶ ሰዒድ ሀብታሙ ባወጣበት ሙከራ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ወልቂጤዎች ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን በረመዳን የሱፍና ሄኖክ አየለ ቢፈጥሩም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

ነገርግን በ65ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ በኃይሉ ተሻገር አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያሬድ ታደሰ ፍፁም በተረጋጋ አጨራረስ በማስቆጠር የወልቂጤን መሪነት ከፍ ማድረግ ችሎ ነበር።


ከሁለተኛዋ ግብ መቆጠር በኋላ የወልቂጤ ከተማዎችን ወደ ኃላ ማፈግፈግ ተከትሎ ወላይታ ድቻዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረው እድሎችን መፍጠር ችለዋል። በዚህም በ74ኛው ደቂቃ ቶማስ ስምረቱ ሳጥን ጠርዝ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት እንድሪስ ሰዒድ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር የበድኑን ተስፋ ማለምለም ችሎ ነበር።

በቀሩት ደቂቃዎች ድቻዎች በቢንያም ፍቅሩና ስንታየሁ መንግሥቱ አደገኛ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ኳሶቹ ለጥቂት ኢላማቸውን መጠበቅ ባለመቻላቻው ጨዋታው በወልቂጤ ከተማዎች የ2-1 የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ