ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ የመጀመርያ ድሉን አሳክቷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ በሀዋሳ ቀጥሎ ዛሬ 4:00 ሰዓት ላይ የተደረገ ሲሆን መከላከያ አዳማ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል፡፡

ማራኪ እና እልህ አስጨራሽ በነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ክለቦች በሜዳ ላይ ለዕይታ ሳቢ የሆነ ፉክክርን ማድረግ ችለዋል፡፡ በቅብብሎሽ የታጀበው ይህ ጨዋታ ለአጥቂዎች በሚደርስ ኳስ ወደ ግብ ክልል በፍጥነት ለመድረስ እጅጉን ታትረዋል፡፡ የመከላከያ በኩል ከኤደን ሽፈራው ከሚገኙ ኳሶች በቀኝ መስመር ወደ ተሰለፈችው ሥራ ይርዳው በመላክ ፈጣኗ ተጫዋች ኳስን በመግፋት ለጓደኞች ስትሰጥ የነበረበት ብልጠት የመከላከያን ጥንካሬን ያጎላ ነበር፡፡ በዚህም ሒደት ከቀኝ መስመር በተገኘ አጋጣሚ ወደ መሀል ባደላ ቦታ በግምት 20 ሜትር ርቀት ላይ 14ኛው ደቂቃ ላይ ዘንድሮ መከላከያን የተቀላቀለችው ሴናፍ ዋቁማ የቀድሞው ክለቧ ላይ የአዳማ ግብ ጠባቂ እምወድሽ ይርጋሸዋ አጋዥ ስህተት ታክሎበት ከመረብ አሳርፋ ጦሩን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡

ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላም መከላከያዎች በስራ ይርዳው ሁለት ተጨማሪ ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝታ ሳትጠቀምበት ቀርታለች፡፡ አዳማ ከተማዎች ኳስን መሠረት አድርጎ ለመጫወት እና ወደ መከላከያ የግብ ክልል በሚሻገሩ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ሁነኛ የፊት መስመር ሜዳ ላይ ይዘው ባለመግባታቸው በተቃራኒው ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ ለመከላከያ የመሐል ክፍል ማማር ተጠቃሽ የነበረችው ህይወት ረጉ ያሳለፈችውን ኳስ አይዳ ዑስማን አስቆጥራ መከላከያ 2 ለ 0 እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ሳቢነቱ ሳይደበዝዝ በቀጠለው ሁለኛው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያው አርባ አምስት የነበረባቸውን ደካማ የማጥቃት ኃይል በተወሰነ መልኩ ቀርፈው የቀረቡበት ቢሆንም የመከላከያን ያህል እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በተለይ የኤደን ሽፈራው ታታሪነት እና የህይወት ረጉ ኳሶች መከላከያዎች ግብ አያስቆጥሩ እንጂ የተዋጣላቸው እንደነበሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ስራ ይርዳው በቀኝ በኩል ብልጠቷን አክላ የሰጠቻትን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ በቀጥታ መታ ግብ ጠባቂዋ እምወድሽ አድናባታለች፡፡

62ኛው ደቂቃ አዳማዎች በጎንዮሽ የቅብብል ሂደት የተገኘች ኳስ ወደ ማዕዘን ምት ወታ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሚያስችላቸውን ግብ አግኝተዋል፡፡ ማዕዘን ምቱን ፀባኦት መሐመድ ስታሻማ ሄለን ሰይፉ በግንባር በመግጨት ያመቻችውን ምርቃት ፈለቀ ወደ ጎልነት ለውጣዋለች፡፡

ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ ከእንቅስቃሴ ውጪ ወደ ጎል ለመጠጋት የሳሱት አዳማ ከተማዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በመከላከያ ተጨማሪ ግብ ሊቆጠርባቸው የሚችሉ በርከት ያሉ ኳሶች የነበሩ ቢሆንም የሴናፍ ዋቁማ የአጨራረስ ድክመት ወደ ግብነት እንዳይለወጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይ አማካዩዋ ህይወት ረጉ (ካኑ) ሦስት ያለቀላቸውን ኳሶች አቀብላት ሴናፍ ሳትጠቀም የቀረችበት አጋጣሚ ምናልባት የመከላከያን የግብ መጠን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች መከላከያ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት የመጀመሪያ ሙሉ ነጥቡን አሳክቷል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት ሴናፍ ዋቁማን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሽልሟታል፡፡

-በጨዋታው ላይ ከታዘብነው መሐል አንዱ የቀይ መስቀል ህክምና ሰጪዎች አለመኖራቸው ነው፡፡በቀላሉ ጉዳት በሚስተናገድበት የሴቶች እግር ኳስ ላይ የህክምና ሰጪ የሆነው ቀይ መስቀል አለመኖሩ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው 80ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ ጠንከር ያለ ጉዳት አስተናግዳ ከሜዳ ስትወጣ በተጫዋቾች እገዛ ያለ ቃሬዛ ታቅፋ ለተጨማሪ ህክምና ከሜዳ የወጣችበትን አጋጣሚ ተመልክተናል፡፡

– በሌላ በኩል ክለቦች ተጫዋቾቻቸው በኮሮና ቫይረስ በስፋት እየተጠቁ በመሆኑ ጥንቃቄን በከፍተኛ ሁኔታ ሊወስዱ ይገባል፡፡ በዛሬው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በድምሩ ሰባት የሚጠጉ ተጫዋቾች በዚህ በሽታ ምክንያት ሜዳ ላይ ሳንመለከት ቀርተናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ