“ከእኔ ሁለት ነገር ከዚህ በኃላ ይጠበቃል”- ጌታነህ ከበደ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በተከታታይ ጨዋታ ድል እንዲያስመዘግብ ጎል በማስቆጠር ለቡድኑ ወሳኝ ተጫዋችነቱን እያስመሰከረ ከሚገኘውን ጌታነህ ከበደ ጋር ቆይታ አድርገናል።

በ2009 ፕሪምየር ሊግ በ25 ጎል በአንድ የውድድር ዓመት ከፍተኛ ጎል በማስቆጠር ባለ ታሪክ ነው። ሁለት ጊዜ ኮከብ ተጫዋች አረና ሦስት ጊዜ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆንም በሊጉ መድመቅ ችሏል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለፉትን አስር ዓመታት በወጥ አቋም ሀገሩን አገልግሏል። በደቡብ ፖሊስ በደደቢት ተጫውቶ ያሳለፈው ጌታነህ በፈረሰኞቹ ቤት በቀየበት ሦስት ዓመታት ከጉዳት ጋር እየታገለ አገልግሏል። በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ጎል በማስቆጠር ወደ አስፈሪነቱ ተመልሷል። በሊጉ ከታዩ ምርጥ ጨራሽ አጥቂዎች ከግባር ቀደምቶቹ መካከል አንዱ እንደሆነ የሚታወቀው ጌታነህ ከበደ ዛሬው በአራተኛ ሳምንት ሰበታ ከተማ ላይ ሁለት ጎል ካስቆጠረበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አግኝተን አዋርተነው ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቶናል።

” ጎል አስቆጥሬ ደስታዬን የገለፅኩበት መንገድ የሥራዬን ውጤን ለማሳየት ነው። የዘራሁትን ነው ዛሬ ያጨድኩት። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳት መስጠት የማስበውን አገልግሎት እንዳልሰጥ እንቅፋት ሆኖብኛል። ዓምና ወደ ጤንነቴ ተመልሼ ጥሩ ማገልገል በጀመርኩበት ጊዜ ደግሞ ሊጉ በኮሮና ምክንያት ተቋረጠ። ዘንድሮ አንድ ነገር ለማድረግ አስቤ ነው የመጣሁት። ለዚህም ከቡድን አጋሮቼ ጋር ጠንክረን በመስራት ስንዘጋጅ ቆይተናል። በተከታታይ ጨዋታዎች ቡድናችን እያሸነፈ እኔም ጎል እያስቆጠርኩ ነው። ይህም በሥራ የመጣ ነው።

“አሁን የማስቀድመው የቡድኑን ውጤት ነው። ከእኔ ሁለት ነገር ከዚህ በኃላ ይጠበቃል። አንደኛው እንደ አጥቂነቴ ጎል ማስቆጠር ግዴታዬ ነው። ይህን ማድረግ አለብኝ። ሁለተኛ የቡድኑ አንበል እንደመሆኔ መጠን በሜዳም ከሜዳም ውጭ ቡድኑን መምራት ይጠብቅብኛል። ይሄን ኃላፊነቴን እወጣለሁ ብዬ አስባለሁ።

“ከአቤል ያለው ጋር ከደደቢት ጀምሮ ጥሩ ጥምረት አለን። በነገራችን ላይ ከአቤል ብቻ ሳይሆን አዲስ ግደይ፣ ጋዲሳ መብራቴ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ከነዓንም ወደ ፊት እየመጣ ይጫወታል። አሁን የሁላችንም ጥምረት አሪፍ ነው። የሚገርማቹሁ ልምምድ ላይ የምናሳየውን 60% ነው በጨዋታ ላይ እያሳየን ያለነው። ከጨዋታ ጨዋታ ራሳችንን እያሻሻልን በልምምድ የሰራነውን 100% በጨዋታ ላይ ስናመጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዚህ በላይ የተሻለ ውጤት ያስመዘግባል።

“ውድድሩ እስካሁን በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው። ደጋፊ ባለመኖሩ ካልሆነ በቀር በዲኤስ ቲቪ መተላለፉ መልካም አጋጣሚ ነው። ውድድሩን ሞቅ አድርጎታል። ከምንም በላይ ተራዘመ፣ ተቋረጠ እና ሌሎች አሰልቺ ነገሮች በዘንድሮ ዓመት እስካሁን አለመኖሩ በጣም ጥሩ ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ