“ሀዋሳ ትልቅ ቡድን ነው፤ ስለመውረድ አይታሰብም” – ብሩክ በየነ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ወሳኝ ድል እንዲያስመዘግብ ብቸኛውን ጎል ካስቆጠረው ብሩክ በየነ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ከሀዋሳ ዓመታዊው የቄራ ሻምፒዮና ውድድር ከተገኘ በኋላ በ2009 በቀጥታ ለወልቂጤ ከተማ ፈርሞ በከፍተኛ ሊግ ተወዳዳሪ በነበረበት ወቅት ድንቅ የውድድር ዓመታትን ማሳለፍ የቻለው ብሩክ ከ2011 ጀምሮ ለሀዋሳ ከተማ በመጫወት ላይ ይገኛል። በተለይ ዓምና በኮቪድ ምክንያት በተሰረዘው የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ ሲፎካካር የእንደነበረም ይታወሳል። በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ ተከታታይ ሁለት ጨዋታ መሸነፉን ተከትሎ ቡድኑ ጫና ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ድሉን እንዲያሳካ እና ቡድኑ እፎይታ እንዲያገኙ ወሳኟን ብቸኛ ጎል ካስቆጠረው ብሩክ በየነ ጋር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አግኝተን አዋርተነዋል።

” ተከታታይ ጨዋታዎችን በመሸነፋችን የነበረብን ጫና ከፍተኛ ነበር። አንደኛ ትንሽ ከበድ የሚሉ ቡድኖች ነበሩ የገጠሙን። ሁለተኛ የተሸነፍነው በአንዳንድ ስህተቶች ነበር። ዛሬ ወደ ድል ለመግባት ከስህተታችን በደንብ ተምረን ነበር የመጣነው፤ ተሳክቶልናል። የማሸነፊያ ጎሉንም በማስቆጠሬ በጣም ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም ይህ ውጤት ለእኛ በጣም ያስፈልገን ነበር። ጎሉ ከሽንፈት እንድናገግም ይረዳናል።

” ጎሉንም አግብቼ ደስታዬን የገለፅኩበት መንገድ፤ ያው ኪዳነ ምህረት ከኔ ጋር ነበረች እና አስቤበት ያደረኩት ነው። ከዚህ በኃላ ቡድኔን ነው መጥቀም የምፈልገው። ጎል ማግባት አለ፤ ማግባት ብዙም ብዙም አያሳስበኝም። ዋናው እኔ የምፈልገው ቡድኔን መጥቀም ነው።

“ሀዋሳ በወጣት የተገነባ ቡድን ነው። ለብዙዎቻችን ትልቅ የመጫወት ዕድል ፈጥሮልናል። ይህ ደግሞ ከድሮ ጀምሮ የመጣ ነው። ትንሽ ልምድ ያላቸው ከአብዛኛው ወጣቶች ጋር በማቀናጀት ይታወቃል። ይህ ደግሞ መቀጠል አለበት። በአካባቢያችን ብዙ ታዳጊዎች አሉ እነርሱም ወደ ፊት የሚመጡ ይሆናል።

“ሀዋሳ ትልቅ ቡድን ነው፤ ስለመውረድ አይታሰብም። አንዳንድ ክፍተቶች ነበረብን። ምክንያቱም ወደ አዲስ አበባ ስንመጣ ዘግይተን ነበር የመጣነው። አየሩ ተፅእኖ አድርጎብናል። አሁን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሻሻልን ነው። ዛሬ ማሸነፋችን የበለጠ ከዚህ በኃላ ጠንክረን እንድንመጣ ያደርገናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ