“ይህ በእግርኳስ ህይወቴ የማረሳው፤ ሁሌም የማስታውሰው ቀኔ ነው” አቡበከር ናስር

በተጠባቂው የሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲረታ ሐት-ትሪክ በመስራት የጨዋታው ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበረው አቡበከር ናስር ስለ ሐት-ትሪኩ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ የውድድር አቀራረብ መካሄድ ከጀመረበት ከ1990 ጀምሮ በሁለቱ የአዲስ አበባ ክለቦች መካከል በተደረጉ 40 የሊግ ጨዋታዎች ሐት-ትሪክ የሰራ ተጫዋች ማግኘች አዳጋች ነው። ምን አልባትም ወጣቱ አጥቂ አቡበከር ናስር ይህን ታሪክ መስራት የቻለ የመጀመርያው ተጫዋች ሳይሆን አይቀርም። ይህን አስመልክቶ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አግኝተነው ሐት-ትሪክ በመስራቱ የፈጠረበትን ስሜት እንዲያጋራን ጠይቀነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

“በሸገር ደርቢ ሐት-ትሪክ በመስራቴ በጣም ደስ ብሎኛል። እውነት ለመናገር በጨዋታው ጎል እንደማስቆጥር እርግጠኛ በመሆን ከጨዋታው አስቀድሞ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሬ ነበር። እስካሁን በሸገር ደርቢ ጎል አስቆጥሬ ስለማላቅ ዛሬ አድነገር እንደምሰራ አስብ ነበር። ፈጣሪም ይመስገን ዛሬ ከአንድ ጎል በላይ ሦስት ጎል አስቆጥሬ ሐት-ትሪክ በመስራቴ በጣም ደስ ብሎኛል። በሀገሪቱ ትልቅ ጨዋታ ሐት ትሪክ መስራት ትልቅ አጋጣሚ ነው። ይህ ለኔ በእግርኳስ ህይወቴ የማረሳው ሁሌም የማስታውሰው ቀኔ ነው። ደጋፊዎቻችን ሲደሰቱ ሳይ በጣም ነው የሚያስደስተው። በቀጣይ ራሴን አዘጋጅቼ ለተሻለ ሥራ እመጣለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ