ከፍተኛ ሊግ | ገላን እና ኤሌክትሪክ አቻ ተለያይተዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሁለተኛ ሳምንት ባቱ ላይ 4:00 ሲጀምር ገላን ከተማን ከ ኤሌክትሪክ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። 

በዚህ ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የቀድሖ ዳኛ ዓለም ነፀበ በተደረገ የህሊና ፀሎት በተጀመረውና ማራኪ እንቅስቃሴ የታየበት የሁለቱ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ያለምንም ግብ ተጠናቋል። በ1ኛው ደቂቃ ገላኖች በአንድ ሁለት ቅብብር ይዘው የገቡትን ኳስ ከማል አቶም በቀላሉ አባከነው እንጂ መሪ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር። ኳስ በመቀባበል ወደ ተጋጣሚያቸው ሦስተኛ ክፍል መግባት እና መቆየት ያልከበዳቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የአደጋ ክልሉን አልፈው ግን ሙከራ ሆነ ግብ ማስቆጠር አልቻሉም።

ከግራ መስመር በሚነሳ እንቅስቃሴ የገላን ቡድን የአብዱለጢፍን ፍጥነት በመጠቀም ለመጫወት የሞከረ ሲሆን በተለይም የኢትዮ ኤሌክትሪክ አማካዮቹ የሚሰሩትን ስህተት ተጠቅሙ ከአንድም ሁለቴ መሪ የሚሆንበትን እድል ማግኘት ችለውም ነበር። በ40ኛው ደቂቃ በአቡዱለጢፍ አማካይነት የሙከሩት ሙከራ በግቡ በቅኝ በኩል አግዳሚውን ጨርፎ ወጥቶበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያው 30 ደቂቃ እጅግ ብልጫን ወስደው መጫወት የቻሉ ሲሆን ገላኖች በተቃራኒው በራሳቸው ሜዳ አፈግፍገው ተጫውተዋል። በዚህም በ58ኛው ደቂቃ ኤርምያስ ኃይሉ ላይ አብዱልለጢፍ ሙራድ በሰራበት ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት የተሻ ግዛው ግብነት በመለወጥ ኤልፓን መሪ ማድረግ ቢችልም ቡድኑ ጎል መሆን የሚችሉ ኳሶችን በማባከኑ ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። ገላኖች በበኩላቸው በመስመር ጥቃቶችን አጥብቀው በመሰንዘር የማታ የማታ አብዱልለጢፍ ሙራድ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የአቻነቷን ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ