የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 4-1 ወላይታ ድቻ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን 4-1 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ውጤቱ

“ውጤቱ ጥሩ ነው። የሚገባንን ሦስት ነጥብ አግኝተናል። እኛን የሚመስል ነገር እያየን ነው። ከዚህ በኃላም ጥሩ ነገር ይገጥመናል ብዬ አስባለሁ።”

ወደ አሸናፊነት መመለሳቸው

“ብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፤ ይህ እግር ኳስ ነው። ከዚህ ቀደም በነበሩ ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቻችን ከእኛ የተሻሉ ስለነበሩ ተሸንፈናል። አሁን ደግሞ እኛ እየተላመድን ሜዳ ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ወደ አሸናፊነት ተመልሰናል። ከዚህ በኃላ ደግሞ የተሻለ ነገር እንሠራለን።”

በቀጣይ ቡድኑ ላይ የሚደረጉ ማስተካከያዎች ካሉ

“በእርግጥ በአሁን ሰአት ማስተካከያ የምንለው ነገር የለም። የሚቀሩን ነገሮች ላይ ልምምዶችን መሥራት ነው። የሊጉ ፉክክር በጣም ከባድ ነው ። በፉክክር ውስጥ ለመገኘት መሥራት ይኖርብናል። አሁንም ብናሸንፍም ሜዳ ላይ ከምናያቸው ነገሮች ተነስተተን ልምምዶችን ጠንክረን መስራት ይኖርብናል።

አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው

“ያው ለጨዋታው ዝግጅት አድርገን ነበር። ነገርግን በመጀመሪያ ደቂቃዎች የገቡብን ግቦች የጨዋታውን መንፈስ ረብሸውብናል። ከዛ በኃላም የገባው ሁለተኛ ጎልን የገባብን ያስተናገድንበት ሒደት በረኛውና ተከላካዮች በተዘናገቡበት ወቅት ነበር። ከዛ በኃላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገን ግብም አስቆጥረናል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ነበርን፤ ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ ልጆቼ ከነገርኳቸው በታች ነበር የተንቀሳቀሱት። ሀዋሳ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ። በዚህም ጥሩ እድሎችን ፈጥረው ከእኛ በተሻለ መጠቀም ችለዋል። እንደ አጠቃላይ የዛሬው ጨዋታ በጥሩ ቡድን ተበልጠን የተሸነፍንበት ነበር።

ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች እቅድ

“ቡድናችን በአብዛኛው በወጣቶች የተገነባ ነው። ለዚህም አዕምሯቸው ላይ ብዙ ሥራዎች መሥራት እንዳለብን ይሰማናል። ተጫዋቹ ወደ ራሳቸው እንዲመለሱ እኛም የቡድኑ ደጋፊዎች ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ