የክልል የውስጥ ሊጎች መካሄድ ጀምረዋል

በኢትዮጵያ ያለው የእግርኳስ እንቅስቃሴ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ በቅርብ ቀናት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊጉ በድጋሚ መጀመር መነቃቃት ጀምሯል። ይህንን ፈለግ ተከትሎም በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ያሉ ክልላዊ የእግርኳስ ውድድሮች የኮቪድ በሽታ መከላከል መርሆችን በተገበረ መልኩ በቅደም ተከተል እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

ከክልል ሊጎች መካከል አንዱ የሆነው የኦሮሚያ ሊግ በአራት ቦታዎች ተከፍሎ መካሄዶ የጀመረ ሲሆን ከዚህ ቀደም ታኅሣሥ ላይ የሰላሌ ውድድር ተጀምሯል። በወለጋው የነቀምት ስታዲየም በምእራብ ሸዋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ቄለም ወለጋ፣ ጊምቢ፣ እና ምስራቅ ወለጋ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ሌላኛው ምድብ ደግሞ ትናንት ጥር 1/2013 የተጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እና ዋና ጸሐፊው ባህሩ ጥላሁን በቦታው በመገኘት ውድድሩን አስጀምረዋል።

በቀጣይ የሌሎች ክልሎች የውስጥ ውድድሮች እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ