የሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ኮከብ ግብጠባቂ ፍሬው ጌታሁን ይናገራል

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እስካሁን በተካሄዱ የስድስት ሳምንት ጨዋታዎች የሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ኮከብ በመባል የተመረጠው ግብጠባቂ ፍሬው ጌታሁን ምርጫውን አስመልክቶ ለድረገፃችን ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል። 

ትውልዱ ሻሸመኔ ከተማ ነው። በዛው የጀመረው የግብጠባቂነት ህይወቱ ጎልቶ መታየት የጀመረው በቀድሞ አጠራር ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ በ2007 ድሬዳዋ በተካሄደው ወድድር ወቅት ለአርሲ ነገሌ በመጫወት ነበር። በወቅቱ ፍሬው ባሳየው ድንቅ ብቃት የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብጠባቂዎች መልማይ የነበረው ንድዝዬ ኤይሚ ምርጫ በ2008 ፈረሰኞቹን ለመቀላቀል ችሏል። በፈረሰኞቹ ቤት በነበው የሁለት ዓመት ቆይታው እምብዛም የፈሰለፍ ዕድል ባያገኝም በገባባቸው ጨዋታዎች ሁሉ አቅሙን ማሳየት ችሏል። በማስከተል ወደ አዲስ አበባ ከተማ፤ ቀጥሎም ወደ ድሬዳዋ ከተማ በማቅናት በቆየባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ የሳምሶን አሰፋ ተጠባባቂ በመሆን መጫወት በቻለባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ያለውን አቅም አሳይቷል። በዚህኛው ዓመት እስካሁን ባለው የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ድንቅ ብቃታቸውን ካሳዩ ግብ ጠባቂዎች መካከል የሚመደበው ፍሬው ዘንድሮ ቡድኑ ወጣ ገባ አቋም ቢያሳይም በግሉ ድንቅ ጊዜ በማሳለፍ የሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጥ ግብ ጠባቂ ተብሎ ከመመረጡ ባሻገር የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሁለት ጊዜያት መካተትም ችሏል። ፍሬውን ከምርጫው በኃላ አግኝተነው ተከታዩን ምላሽ ሠጥቶናል።

” በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታዬ ለኔ ትምህርት ቤት የገባው ያህል ነው የማስበው። በትልቅ ቡድን ከፍተኛ ልምድ ካላቸው ግብጠባቂዎች እና አሰልጣኝ ጋር መስራቴ ለኔ ከፍተኛ ጥቅም አግኝቼበታለሁ። የመጣሁት ዝቅተኛ ከሆነ ሊግ ነው። የማላውቃቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ፤ ብዙ ነገር ተምሬበታለሁ። በአንዴ የመሰለፍ ዕድል ለማግኘት እንደማልችል አውቅ ነበር። ያም ቢሆን በተገኘው አጋጣሚ ራሴን ለማሳየት እሞክር ነበር። በአጠቃላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታዬ ብዙ ትምህርቶች እና ልምድ ያገኘሁበት ነበር። በጊዮርጊስ ቤት የተማርኩትን ትምህርት አሁን እየተገበርኩት ነው። በቅዱስ ጊዮርጊስ ትንሽ ብቆይ የመጫወት ዕድሉን አገኛለሁ ብዬ አስብም ነበር።

“ድሬደዋ ስመጣ ማንም እንደሚያውቀው ሳምሶን አሰፋ ትልቅ ልምድ ያለው እጅግ ጎበዝ በረኛ ነው። በአንዴ እርሱን አስቀምጦ ወደ ቋሚ ተሳላፊነት መምጣት ከባድ ነው። ዕድሉን እስክታገኝ ድረስ በትዕግስት መጠበቅ ያስፈልግ ነበር። አልፎ አልፎ በማገኛቸው የመጫወት ዕድሎች ሁሉ በአግባቡ ለመጠቀም የተቻለኝን ጥረት አድርግ ነበር። ይህንንም በትዕግስት ጠብቄ አሁን የቡድኑ ቋሚ ግብጠባቂ መሆን ችያለው።

“እስካሁን ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ። አሁን ያለኝ አቋም የመጣው በሥራ ነው ብዬ አስባለው። አንዳንዴ ሰርተህም አዕምሮህ ንፁህ ካልሆነ ላይሳካ ይችላል። አዕምሮህን ንፁህ አድርገህ የምትሰራ ከሆነ ዕድሉን ስታገኝ ያሰብከውን ወደ ተግባር ትቀይራለህ። ዕውነት ለመናገር ዘንድሮ በደንብ ነበር ራሴን ሳዘጋጅ የቆየሁት በቀን ተደጋጋሚ ልምምዶችን እሰራ ነበር። ያ ይመስለኛል እስካሁን ባለው የስድስት ሳምንት ቆይታ ጥሩ ነገር ማሳየት የቻልኩት። በሚቀጥሉ ጨዋታዎችም የነበሩብኝን ድክመቶች በማስተካከል ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን ጥሩ ነገር ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ።

” ማንኛውም በዓለም ላይ የሚገኝ ተጫዋቾች ሁሉ ከምንም በላይ ብሔራዊ ቡድን መመረጥን ይመኛሉ። እኔም በዚህ መልኩ በብሔራዊ ቡድን በመጠራቴ ትልቅ ክብር ተሰምቶኛል። መመረጤ አንድ ነገር እያደረኩ እንደሆነ እንዲሰማኝ እና በራስ መተማመኔ የበለጠ እንዲጨምር ያደርገዋል። መጠራቴ ብቻ በቂ አይደለም። የበለጠ ጠንክሬ የተሻለ ነገር የመስራት ኃላፊነት እንዳለብኝ ነው የማስበው። መመረጤ ከምንም በላይ በጣም ደስ ብሎኛል። ለረጅም ዓመታት ስመኘው እና ስጠብቀው የነበረ በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል ኩራትም ተሰምቶኛል።

” ኢትዮጵያውያን ግብጠባቂዎች ራሳችንን ዝቅ አድርገን የመግባት ችግር አለ። ብዙ የውጭ ግብጠባቂዎች ከዚህ ቀደም መብዛታቸው በእኛ ላይ ያሳደረው ተፅእኖ አለ። ሁሌም ለራሳችን የምንሰጠው ግምት ከፍ ማድረግ አለብን። አሁን ላይ የውጭ ግብጠባቂዎችን ስታይ ጥሩ አይደሉም። በዛ ላይ ቁጥራቸው እየቀነሰ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ግብጠባቂ ራሱን ለማሳየት አጋጣሚው ጥሩ ስለሆነ የበለጠ ዕሎችን ለመጠቀም ጠንክረን መስራት አለብን።

” በሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጥ ግብጠባቂ ሆኜ በመመረጤ ትልቅ ስሜት ነው የተሰማኝ። ምክንያቱም የሥራዬን ውጤት ነው እያየሁት ያለሁት። መመረጤ በስራዬ እንደሆነ አስባለሁ። ይህ ደግሞ መሆኑ የበለጠ ከዚህ በኃላ መሥራት እንዳለብኝ እረዳለሁ።

“በመጨረሻ ከድሬዳዋ ጋር ጥሩ ዓመት በማሳለፍ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ውጤት ይዞ እንዲያጠናቅቅ ትልቅ ምኞት አለኝ። በድሬደዋ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከዚህ የተሻለ ቡድናችንን ውጤታማ ለማድረግ እጥራለሁ። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ