የጌታነህ ከበደ ታሪካዊ አጋጣሚ…

የ2013 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የተለያዩ አዳዲስ ኹነቶችን እያስመለከተን ሰባተኛ ሳምንት ሲደርስ በዛሬው ዕለትም ታሪካዊ አጋጣሚ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት አስመልክቶናል።

በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ለኢትዮጵያ እግርኳስ በርከት ያሉ ቱሩፋቶችን ይዞልን እንደመጣ በተለያዩ አጋጣሚዎች እያስመለከተን ይገኛል። በዛሬው ዕለት በሰባተኛው ሳምንት የጅማ አባ ጅፋር ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 ከማሸነፉም በላይ በጨዋታው ላይ ልዩነት በመፍጠር ጌታነህ ከበደ ሐት-ትሪክ መስራቱ ይታወቃል። በሌላው ዓለም እንደተለመደው ሐት ትሪክ የሰራ ተጫዋች ከዕለቱ ዋና ዳኛ ኳሱን በመውሰድ የግላቸው እንደሚያደርጉ ይታወቃል። ወደ እኛ ሀገር የእግርኳስ ስንመጣ ግን እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች እንዳልተለመዱ የሚታወቅ ነው። በዘንድሮ ዓመት በሙጅብ ቃሲም የጀመረው ሐት-ትሪክ መስራት በአበቡበከር ናስር ቀጥሎ ለማየት ብንችልም ሐት-ትሪክ የሰሩብት ኳስ ይዘው ሲወስዱ አልተመለከትንም። ሆኖም ግና ዛሬ በታሪክ አጋጣሚ ጌታነህ ከበደ በዕለቱ ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ሐት-ትሪክ የሰራበትን ኳስ ተረክቦ የግሉ በማድረግ አዲስ ክስተት ተፈጥሯል።

የዚህ ታሪክ አጋጣሚ ባለቤት የሆነው ጌታነህ ስለ ሁኔታው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።

“በኢትዮጵያ እግርኳስ ረዘም ላለ ዓመት እንደመጫወቴ ሐት-ትሪክ ሰርቼ ኳሱን ይዤ የሄድኩበት አጋጣሚ የለም። ደቡብ አፍሪካ በነበርኩበት ጊዜ ሐት-ትሪክ ባለመስራቴ እንዲህ ዐይነት ዕድል ያላገኘው ቢሆንም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጁቡቲ ጋር ስንጫወት አራት ጎል አስቆጥሬ ኳሱን መውሰዴን አስታውሳለው። ዛሬ ሦስት ጎል ማግባቴ ኳሱ ተሰጥቶኛል። ይህ መሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል። በቀጣይ መለመድ ያለበት ነገር ነው። የኳስ እጥረት አለ እየተባለ መቅረት የለበትም። በውጭ ሀገር የምናየው እኛም ሀገር መኖር አለበት። የጎለሎቹ መታሰቢያነትም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ይሁንልኝ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ