ሪፖርት | ፋሲል አዳማን በሰፊ ልዩነት ረትቷል

ፋሲል ከነማ ከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ ባሳየበት ጨዋታ አዳማ ከተማን 4-0 ማሸነፍ ችሏል።

ሁለቱም ተጋጣሚዎች በሰባተኛው ሳምንት ካደረጓቸው ጨዋታዎች አንድ አንድ ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ፋሲል ከነማ በይሁን እንዳሻው ቦታ በዛብህ መለዮን ሲጠቀም አዳማ ደግሞ ዘሪሁን ብርሀኑን በሙጃይድ መሐመድ ተክቷል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ለማመን የሚከብዱ ኳሶች የተሳቱበት ነበር። ጨዋታው እንደጀመረ ከወትሮው የተለየ ንቃት ያሳዩት አዳማዎች በፍሰሀ ቶማስ ፣ በቃሉ ገነነ እና የኋላሸት ፍቃዱ አማካይነት እምብዛም ከባድ የማይባሉ ሙከራዎች አድርገዋል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግን እንደ አጀማመራቸው ኳስ ይዘው ወደ ፋሲል ሜዳ ከመግባት ይልቅ ለመልሶ ማጥቃት የቀረበ አጨዋወትን ሲከተሉ ተስተውለዋል። ፋሲሎችም ከተከላካይ መስመር በቀጥታ የሚጣሉ ኳሶችን አማራጭ የማጥቂያ መንገድ አድርገው መውሰዳቸው አልቀረም።

14ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን ከግራ አሻምቶት ሳሙኤል ዮሃንስ ለጥቂት በሳተው ኳስ ወደ ግብ መቅረብ የጀመሩት ፋሲሎች የአዳማን ብልጫ ሙሉ ለሙሉ ወደ ራሳቸው ባይቀለብሱም እንቅስቃሴውን ተመጣጣኝ አድርገውታል። የመስመር አማካያቸው ሽመክት ጉግሳ በሚያደርገው እንቅስቃሴ በተለይም የአዳማው የመስመር ተከላካይ ታፈሰ ሰረካ ተጎድቶ ከወጣ በኋላ ተደጋጋሚ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ታይተዋል። ከ19ኛው ደቂቃ የሱራፌል የርቀት ሙከራ በኃላ ሽመክት ከበዛብህ እና ከአምሳሉ በደረሱት ኳሶች ሁለት ጊዜ ሳጥን ውስጥ የገባባቸው አጋጣሚዎች ፋሲልን ለግብ ቢያቀርቡትም በማይታመን መልኩ ሙከራዎቹ ወደ ውጪ ወጥተዋል። በተመሳሳይ ፍሰሀ ቶማስ እና በተለይም ታፈሰን ቀይሮ የገባው አብዲሳ ጀማል ከግብ አፋፍ ላይ አዳማን መምራት የሚያስችሉ ሦስት ኳሶችን ወደ ውጤት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲል አዳማዎች የታፈሰን ቦታ እንዲሸፍን ያደርጉት ጀሚል ያዕቆብም ተጎድቶባቸው አምሳሉ መንገሻን በማስገባት ሁለተኛ አስገዳጅ ቅያሪ አድርገዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ሳጥኑ መግቢያ ላይ ከነጠቁት ኳስ ግብ ስር የደረሱት ፋሲሎች ከእንየው ካሳሁን በተነሳ እና ፍስሐ ቶማስ በእጅ በነካው ኳስ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ አጋጣሚውን ወደ ግብነት ቀይሮ ፋሲልን ቀዳሚ ያደረገው ሙጂብ ቃሲምም ደስታውን ባለመግለፅ ለቀድሞው ክለቡ ያለውን ክብር አሳይቷል። በቶሎ ግብ ይቆጠርበት እንጂ ይህኛው አጋማሽ ላይም ያለቁላቸው ኳሶች መሳታቸው አልቀረም። 60ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት በቅብብል ሳጥን ውስጥ የገቡት ፋሲሎች የመጨረሻ የግብ ዕድል ቢፈጥሩም ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ያደረገው ሙከራ በዳንኤል ተሾመ መክኗል። 66ኛው ደቂቃ ደግሞ የአዳማው የኋላሸት ፍቃዱ በግራ መስመር ጎል ለመሆን የሚችል ጥሩ ኳስ ቢያገኝም ሙከራው ወደ ውጪ ወጥቷል።

የጨዋታውን ሚዛን በአዳማ ሜዳ ላይ እንዲያጋድል ያደረጉት ፋሲሎች ከፍተኛ ብልጫ ባሳዩባቸው የመጨረሻ ደቅቃዎች ተከታታይ ግቦችን አስቆጥረዋል። 76ኛው ደቂቃ ላይ የከፈቱት ጥቃት በአዳማዎች ሲመለስ ተቀይሮ የገባው ይሁን እንዳሻው ከሳጥኑ መግቢያ ላይ አግኝቶ በቀጥታ በመምታት ሲያስቆጥር ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ ከእንየው ካሣሁን ከተነሳ እና በኋላሸት ፍቃዱ በእጅ በተነካ ኳስ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው መጂብ ማስቆጠር ችሏል። በግቦቹ ይበልጥ ጫና ውስጥ የገቡት አዳማዎች ለመከላከል ጥረት ቢያደርጉም ሰፋፊ ክፍተቶች መተዋቸው አልቀረም። 83ኛው ደቂቃ ላይም እንየው ከመስመር ያሻገረውን ሙጂብ አመቻችቶለት ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ አራተኛ ግብ አስቆጥሮባቸል። አዳማዎች የጨዋታው ማብቂያ ላይ ያገኙትንም የፍፁም ቅጣት ምት ፍሰሀ ቶማስ ወደ ጎልነት መቀየር ሳይችል ጨዋታውን በ 4-0 ተሸናፊነት ደምድመዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ