ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ጅማ አባ ጅፋር

የስምንተኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከተው ዳሰሳችንን እንዲህ አሰናድተነዋል።

ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በሸገር ደርቢ ድል ከተጎናፀፈ 15 ቀናት በኋላ ወደ ሜዳ ይመለሳል። ሁለት ተከታታይ ድሎችን አሳክቶ የነበረው ቡድኑ በነበረበት መነሳሳት ላይ ሆኖ ቀጣይ ጨዋታዎቹን በዛው ቢያደርግ የተሻለ የነበረ ቢሆንም ካለው የጨዋታ መደራረብ አንፃር ዕረፍቱም ከተጋጣሚው በተሻለ የአካል ብቃት ላይ ሆኖ ወደ ሜዳ እንዲገባ የሚያግዘው ነው።

በነገው ጨዋታ ቡና ሽንፈት ባስተናገደበት የሀዋሳው ጨዋታ ዓይነት የተጋጣሚ አቀራረብ ሊገጥመው ይችላል። በመሆኑም የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡድን በጠባብ ክፍተቶች ውስጥ ቅብብሎችን በመከወን እና ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ያለው ጥንካሬ እንደሚፈተሽ ይጠበቃል። አማካይ መስመር ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው እየጎላ ከመጡት ዊሊያም ሰለሞን እና ሬድዋን ናስር በተጨማሪ ክፍተቶች ሲጠፉ ወደ ኃላ በጥልቀት እየተመለሰ የተጋጣሚን አቋቃም ለማዛባት የሚጥረው ታፈሰ ሰለሞን ታታሪነት ለሦስትዮሹ የቡድኑ የፊት መስመር ጥምረት ዕድሎች መከፈት እጅግ ወሳኝ ይሆናል። በጨዋታው ቡና በተለይም ከኃይሌ ገብረትንሳይ የቀኝ መስመር በኩልም የጅማን የኋላ ክፍል ሰብሮ ለመግባት ጥረት እንደሚያደርግ ይታሰባል። ቡድኑ ጉዳት ላይ የነበሩት አማኑኤል ዮሃንስ እና ሚኪያስ መኮንን ጨምሮ ሙሉ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኖለታል።

ጅማ አባ ጅፋር አሁንም ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ሌላ ከባድ ጨዋታ ያደርጋል። ከአንድ ቀን በፊት አሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ቡድኑን ትተው መሄዳቸውን ተከትሎ ሌላ አነጋጋሪ ክስተት ውስጥ የገባው አባ ጅፋር በምክትል አሰልጣኙ የሱፍ ዓሊ አማካይነት ልምምዱን ሲያከናውን ቆይቷል።

በጥብቅ መከላከል ላይ ተመስርቶ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር በማሰብ ወደ ሜዳ መግባት ከጀመረ ጀምሮ መጠነኛ መሻሻል ያሳየው ጅማ የሚታዩበትን ተደጋጋሚ ችግሮች ማስተካከል ግን አልቻለም። በተለይም በተከታታይ ከቆሙ እና ከተሻጋሪ ኳሶች ጎሎችን ሲያስተናግድ መታየቱ ለጥንቃቄ ከሰጠው ትኩረት ጋር የማይጣጣም ሆኗል። የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚን በመጠቀሙ በኩልም አመርቂ የሚባል ለውጥ ባያሳይም እንደ ሮባ ወርቁ እንዲሁም ቤካም አብደላ ዓይነት ተጫዋቾች በግል ጥረታቸው ያስቆጠሯቸው ጎሎች የጨዋታ ፉክክር ውስጥ እንዲቆይ ሲያስችሉት ተመልክተናል። ነገም ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ከሚይዘው ተጋጣሚው ጀርባ ለመግባት መሰል የግል ብቃቶች ጎልቶ መውጣት ላይ ተስፋ የሚያደርግ ይመስላል። ከዚያ በፊት ግን ቡድኑ በሙሉው የጨዋታ ጊዜ የተሳካ የመከላከል ቅርፅን በመያዝ ስህተቶችንም በመቀነስ መጫወት የግድ ይለዋል። በምክትል አሰልጣኙ እየተመራ ጨዋታውን እንደሚያደርግ የሚጠበቀውን የጅማን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለአራት ጊዜያት ተገናኝተው ጅማ ሁለቴ ሲያሸንፍ ቡና አንዴ ድልን አሳክቷል። አንዱን ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ጅማ አራት ግቦችን ማስቆጠር ሲችል ቡና ደግሞ ሁለት ግቦች አሉት።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማሪያም ሻንቆ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – ሬድዋን ናስር – ዊሊያም ሰለሞን

አቤል ከበደ – አቡበከር ናስር – ሀብታሙ ታደሰ

ጅማ አባ ጅፋር (4-4-2)

ጃኮ ፔንዜ

ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ –ከድር ኸይረዲን – ኤልያስ አታሮ

ሳምሶን ቆልቻ – ሱራፌል ዐወል – ንጋቱ ገብረስላሴ– ሙሉቀን ታሪኩ

ሮባ ወርቁ – ተመስገን ደረሰ


© ሶከር ኢትዮጵያ