የአሠልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 3-1 ጅማ አባጅፋር

አራት ግቦች ከተስተናገዱበት የኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባጅፋር ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች የድህረ ጨዋታ አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል። 

ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው…

ጅማዎች በእኛ ሜዳ አንድ ተጫዋች ብቻ ልከው እንድንጫወት ፈቅደውልናል። ግን መሐል ሜዳውን አልፈን ስንሄድ ቁጥራቸውን አብዝተው ለመከላከል ሞክረዋል። በዚህ እንቅስቃሴ ደግሞ ማንኛውም ቡድን ወደ ጎሉ ሲጠጋ እያጠበበ ነው የሚከላከለው። ከዚህ መነሻነት የክንፍ ቦታዎች ይከፈታሉ። እኛም እነዚህን ክፍት ቦታዎች ግምት ውስጥ ከተን ተጫውተናል። ይህንን ብልም ግን እነዛን ክፍት ቦታዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በደንብ አልተጠቀምንበትም ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ይህንን ለማረም ጥረት አድርገናል።

ቡድኑ ውስጥ ስላለው ጉጉት…

በቡድን ውስጥ ያለው ጉጉት ተነሳሽነት ይፈጥራል። ግን የምንፈልገውን ነገር እስከሚያጠፋ ድረስ መሄድ የለበትም። ጨዋታውን ለማሸነፍ እና የማሸነፍ ጉዟችንን አስጠብቆ ለመሄድ ያለው የመጓጓቱ ስሜት ነገሮችን እንዳናስተውል ያደርገናል። ይህንን ማረም አለብን። ይህንን ብልም ግን ፍላጎቱ እና ጉጉቱ ያስፈልጋል። ምክንያቱም በጎ ጎን ስላለው።

አሥራት ቱንጆ ስላስቆጠራት ጎል..

ኳስን ተከትሎ መሄዱ ጥቅሙ ይሄ ነው። ምክንያቱም እንቅስቃሴ ይዞህ ስለሚሄድ ከጎንህ ያለውን ሰው መረዳት እና እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎችን የማግኘት እድል ታገኛለህ። አስራትም በጨዋታው እንቅስቃሴ ነው በዛ ቦታ የተገኘው።

ዩሱፍ ዓሊ – ጅማ አባጅፋር (ምክትል አሠልጣኝ)

ይዘውት ስለገቡት የጨዋታ እቅድ…

በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ የምንጠብቀውን ነገር ባናገኝም አብዛኛውን የሜዳችንን ክልል አስጠብቀን ለመውጣት አስበን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ በ4-4-2 የተጨዋች አደራደር ቅርፅ እድሎችን ለመፍጠር ነበር ያሰብነው። ነገርግን ያገኘናቸውን እድሎች ሳንጠቀም ግብ አስተናግደን ተሸንፈናል።

ቡድኑ ስላመከናቸው የግብ ማግባት እድሎች…

ሦስት ነጥብ ለመያዝ ጉጉት ነበረን። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀማችን ግን ዋጋ አስከፈለን። ካገኘናቸው ሁለት ንፁህ አጋጣሚዎች አንዱን እንኳን ብንጠቀም የተሻለ ነገር ይገጥመን ነበር። ግን አጋጣሚውን ባለመጠቀማችን ዋጋ ከፍለናል።

ተጫዋቾቹ ስለነበራቸው ጉጉት…

ጉጉቱ ከውጤት ፍለጋ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ሌላ ምንም ነገር የለውም።

ቡድኑ ላይ ጫናዎች…

እንደሚታወቀው ታዳጊ ልጆች ላይ ነው እየተጠቀምን ያለነው። የተወሰኑት ተጫዋቾች ደግሞ በኮቪድ-19 ሜዳ ላይ አልነበሩም። ይህ ክፍተት ደግሞ ጫና ፈጥሮብናል። በተለያዩ ምክንያቶች በፈለግነው መንገድ ተጫዋቾቻችንን እንዳናገኝ አድርጎናል። 


© ሶከር ኢትዮጵያ