ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎቹን ማክሰኞ፣ ረቡዕ እና ሐሙስ አከናውኗል። የተካሄዱት ጨዋታዎች ተንተርሶ ዋና ዋና ክለብ ተኮር ጉዳዮችንም እንዲህ ቀርበዋል።

👉ዐፄዎቹ መሪነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን በመርታት የሰንጠረዡን አናት የተረከቡት ዐፄዎቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው እና አስከፊ ግስጋሴ እያደረገ የሚገኘው አዳማ ከተማን ገጥመው 4-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

በሙሉ ዘጠና ደቂቃዎች የተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር የነበራቸው ፋሲል ከነማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ እንደነበራቸው የጨዋታ ቁጥጥር በቂ የጠሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች እና የቅርፅ ለውጥ ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች ሙጂብ ቃሲም ሁለት ጎሎችን ከፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ተቀይረው የገቡት ይሁን እንደሻው እና ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ባስቆጠሯቸው ግቦች አዳማ ከተማ በሰፊ የግብ ልዩነት መርታት ችለዋል።

በሊጉ ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ ከሆኑ ቡድኖች አንዱ የሆነው ፋሲል ከነማ በአስደናቂ አቋም ላይ የሚገኘው አጥቂያቸው ሙጂብ ቃሲም አበርክቶ እንዳለ ሆኖ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስተው ውጤት መቀየር የሚችሉ ተጫዋቾችን ያካተተ ስብስቡ፣ ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ የመጣው የተሰላፊዎቹ ብቃት እንዲሁም አሰሰልጣኝ ሥዩም በጨዋታ ወሳኝ ወቅቶች ላይ እያሳዩ የሚገኙት ውጤታማ የታክቲክ እና የተጫዋች የለውጥ ውሳኔዎች ቡድኑ ከጨዋታዎች ድል እያጣጣመ እንዲጓዝ አስችለውታል።

ሊጉን በ19 ነጥብ እና በ10 ንፁህ ግቦች እየመሩ የሚገኙት ፋሲሎች መሪነታቸውን አስጠብቀው ለመጓዝ በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ከመሪዎቹ ተርታ የተሰለፉ ቡድኖችን የሚፈትነው ወልቂጤ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል።

👉አባካኙ ኢትዮጵያ ቡና ተጨንቆም ቢሆን ድል አድርጓል

በ8ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሁለት ሳምንት የሚጠጋ እረፍት በኃላ ጅማ አባጅፋርን የገጠሙት ኢትዮጵያ ቡናዎች የተገኙ ዕድሎችን በአግባቡ ወደ ግብነት መቀየር ባለመቻል ኋላ ላይ ራሳቸውን ለአላስፈላጊ ውጥረት ዳርግው የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻም ድል አድርገዋል።

በ90 ደቂቃ በሁሉም ረገዶች ከተጋጣሚያቸው ተሽለው መገኘት የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገኟቸውን የግብ እድሎችን በአግባቡ ወደ ግብነት መቀየር አለመቻላቸው ዋጋ ሊያስከፍላቸው ተቃርቦ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ አቡበከር ናስር በ22ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ መምራት የጀመሩት ቡናዎች የአንድ ቡድን የበላይነት በተስተዋለበት ጨዋታ በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በጨዋታው ተቸግረው የነበሩት ጅማዎች በ57ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ወንድሜነህ ደረጀ በሰራው ጥፋት በተገኘች የፍፁም ቅጣት ምትን ወደ ግብነት ቀይረው ወደ ጨዋታው መመለስ ችለው ነበር። ከአቻነት ግብ መቆጠር በኃላ የተነቃቁት ጅማዎች መጠቀም አልቻሉም እንጂ ሁለት እጅግ አስቆጭ ሙከራዎችን በብዙዓየሁ እንደሻው እና ንጋቱ ገ/ስላሤ አግኝተው መጠቀም ባለመቻላቸው ቡናዎች ላይ ያልተጠበቀ ድል ለመጎናፀፍ አቃርቧቸው ነበር። የኋላ ኋላ ተረጋግተው ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ81ኛው እና 87ኛው ደቂቃ አሥራት ቱንጆ እና ዊልያም ሰለሞን ባስቆጠሯቸው ግቦች ጨዋታውን 3-1 አሸንፈው ለመውጣት ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን ወደ 16 በማሳደግ ከሀዲያ ሆሳዕና በግብ ክፍያ በልጦ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለው ኢትዮጵያ ቡና በትናንቱ ጨዋታ ላይ የነበረው የአባካኝነት ሁኔታን ካልቀረፈ በቀጣይ ጫናዎች በሚበዙባቸው ጨዋታዎች ላይ እንዳይቸገር የሚያሰጋ ነው። በተጨማሪም በጥሩ ሁኔታ ሲያስኬዱት የነበረው ጨዋታ በጅማ አጥቂዎች ደካማ አጨራረስ ምክንያት ከእጃቸው ለመውጣት ተቃርቦ የነበረ መሆኑ ሲታይ በድንገተኛ ቅፅበቶች የሚገኙ አጋጣሚዎችን በዋዛ የማያሳልፉ አጥቂዎች ብሎም ቡድኖች ሲገጥሟቸው በምን መልኩ ይወጧቸዋል ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ኮስታራነት በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ይጠበቅባቸዋል።

👉ሀዲያ ሆሳዕና ከሽንፈት አገግሟል

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ ያለመሸነፍ ጉዞው የተገታው ሀዲያ ሆሳዕና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ሳሊፉ ፎፋና በ4ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በመርታት ከሽንፈት ያገገመበትን ወሳኝ ድል አሳክቷል።

ከፍተኛ አካላዊ ግጭቶች እና ጉሽሚያዎች የተስተዋሉበት ጨዋታው በጣት የሚቆጠሩ የግብ ሙከራዎች የተስተናገዱበት ነበር። ገና በማለዳው ፎፉና በግል ጥረቱ ባስቆጠራት ግብ የልባቸው የደረሰ የመሰሉት ሀዲያዎች እንደ ቀደሙት ጨዋታዎች በነፃነት አጥቅተው ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ከመጫወት ይልቅ በጥንቃቄ በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት ጥሬት ፍሬያማ አድርጓቸዋል። ዋንኛ ተሰላፊዎቹ ከጤና መታወክ ተመልሰው እንደመጫወታቸው እና ቡድኑ ከሽንፈት በኋላ ያደረገው ጨዋታ እንደመሆኑ ሦስት ነጥብ ከድሬዳዋ ለመውሰድ አሰልጣኝ አሸናፊ ይዘውት የገቡት አቀራረብ አዋጭ የሚጠበቅ እንደሆነ እዚህ ጋር ማንሳት ግድ ይላል።

በዚህ ውጤት ሀዲያ ሆሳዕና በ16 ነጥብ በኢትዮጵያ ቡና በርካታ ግብ በማስቆጠር ተበልጠው በሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት በአስደናቂ ሰሞነኛ ግስጋሴ ላይ የሚገኘውን ሀዋሳ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል።

👉ቅዱስ ጊዮርጊስ ተቸግሮም ቢሆን አሸንፏል

በ8ኛ ሳምንት የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲሱ አሰልጣኛቸው ዘላለም ሽፈራው ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመሩት ወላይታ ድቻዎች ከባድ ፈተና ቢገጥማቸውም ጨዋታው መጠናቀቂያ ሲቃረብ ሳልሀዲን ሰዒድ ባስቆጠራት ግሩም የጭንቅላት ኳስ አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

በቁጥር በርከት ብለው ሲከላከሉ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ከመስመር ሆነ በቀጥተኛ አጨዋወት ይሰነዘሩባቸው የነበሩትን የቅዱስ ጊዮርጊሶችን ጥቃት በቀላሉ ሲመክቱ በተስተዋለበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሳልሀዲን ሰዒድን ቀይረው ወደ ሜዳ ካስገቡ ወዲህ የተነቃቁት ፈረሰኞቹ በስተመጨረሻም በ83ኛው ደቂቃ ሳልሀዲን ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ለፈረሰኞቹ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን እንዲያስመዘግቡ አስችሏል።

በሊጉ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን የያዘው ቡድኑ በዚህ ሳምንት ሁሉንም የተጠቀመ ሲሆን እጅግ ጠንካራ በሆነ አደረጃጀት ክፍተት አሳጥቶ ሲከላከል የነበረው ድቻን በሁሉም አይነት የማጥቃት ስልቶች ተጠቅመው ለማስከፈት ባደረጉት ጥረት ከአንደኛው ያጡትን በሌላኛው አግኝተው በመጨረሻም አስፈላጊዋ እና ጣፋጯ ሦስት ነጥብን ማሳካት ችለዋል።

በአስራ አምስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሻለው ባህር ዳር ድል አድርጓል

ከሰሞኑ ይጠቀሙት ከነበረው የመጀመሪያ ተመራጭ ተሰላፊዎች የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገው ሰበታ ከተማን የገጠሙት ባህርዳር ከተማዎች በአወዛጋቢ ክስተቶች በታጀበው ጨዋታ ከመመራት ተነስተው በሁለተኛው አጋማሽ አራት ግቦችን አስቆጥረው ሰበታ ከተማን 4-1 መርታት ችለዋል።

ሁለት ኳስን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ ቡድኖችን ባገናኘው ጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱ ቡድኖች በኩል የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለመውሰድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ፍፁም ገ/ማርያም ባስቆጠራት ግብ መምራት የጀመሩት ሰበታዎች ጨዋታውን ይበልጥ ለመቆጣጠር በማለም የተከላካይ አማካዮን ዳንኤል ኃይሉን በዳዊት እስጢፋኖስ መተካታቸው ያለሙትን የጨዋታ ቁጥጥር ከማስገኘት ይልቅ ለባህር ዳር ከተማዎች መልካም እድልን ይዞ ብቅ ብሏል።

ከዳንኤል ሀይሉ መውጣት በኃላ የባህርዳር ከተማው ቁልፍ ሰው ፍፁም ዓለሙ ጨዋታዎችን ለመወሰን አጥብቆ የሚፈልገውን በተጋጣሚ ቡድኖች የተከላካይ እና አማካይ ተሰላፊ ተጫዋቾች መካከል የሚገኘውን ክፍተት በነፃነት የመጠቀም ዕድልን ማግኘቱ በርካታ የጎል ዕድሎችን እንዲፈጥር አስችሎታል። በዚህም በተገኙ ጎሎች ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ረድቶታል።

ባህር ዳር ከተማዎች በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች በአጨዋወት እና በተጫዋቾች ምርጫ የነበራቸውን ተመሳሳይ አቀራረብ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች መቀያየር መጀመራቸው ታይቷል። ይህም ከሞላ ጎደል ውጤት ማስገኘቱ እየታየ የሚገኝ ሲሆን ከሦስት ጨዋታ ሁለቱን ድል እንዲያደርጉበት አስችሏቸዋል።

👉ሰበታ ከተማ ከድል እንደተራራቀ ቀጥሏል

በ2ኛ የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን 3-1 ከረቱ ወዲህ ሰበታ ከተማዎች ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በሦስቱ አቻ ተለያይተው በአንፃሩ በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፈው በስድስት ነጥቦች በአስረኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

እርግጥ ነው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በባህርዳር ከተማ 4-1 በተረቱበት ጨዋታ የውጤት ማሳያው አንድ አቻ ላይ በነበረበት ወቅት መሪ ሊሆኑበት የሚችሉትን ግብ ፍፁም ገ/ማርያም ቢያስቆጥርም በእለቱ ዳኞች ከጨዋታ ውጭ በመባል መሻሩ ያሰደረባቸው የስነ ልቦና ተፅዕኖ እንዳለ ቢታመንም ከሰሞኑ እያስመዘገበ የሚገኘው ውጤት አመርቂ አይደለም።

ምንም እንኳን ቡድኑ እንደ ጅማ አባ ጅፋር ሁሉ ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች የቡድኑ አባላት እና የክለቡ አመራሮች ሰጣ ገባ ውስጥ ቢገኝም እንደያዘው ስብስብ እና እንደ አሰልጣኙ የጥራት ደረጃ እስካሁን እያስመዘገበ የሚገኘው ውጤት ቡድኑን የሚመጥን አይደለም።

ይህን ውጤት አልባ ጉዞ ለመቀልበስ ሰበታ ከተማ በ9ኛው ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ እንደ እነሱ ሁሉ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ሲዳማ ቡናን የሚገጥሙ ይሆናል።

👉ሀዋሳ ከተማ በመልካም ግስጋሴው ቀጥሏል

በውድድሩ ጅማሮ አስከፊ አጀማመርን ያደረገው ሀዋሳ ከተማ ከሦስተኛው ሳምንት አንስቶ በተከታታይ ጥሩ ውጤቶችን በማስመዝገብ ደረጃውን እያሻሻለ ይገኛል።

በዚህኛው ሳምንት የከተማ ተቀናቃኛቸው ሲዳማ ቡናን የገጠሙት ሀዋሳ ከተማዎች ፍፁም ተቃራኒ በነበሩ የሁለት አጋማሾችን ቢያሳልፉም በጨዋታው መጀመሪያ እና መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ብሩክ በየነ እና መስፍን ታፈሰ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ሲዳማ ቡናን መርታት ችለዋል።

በመጀመሪያ አጋማሽ አጥቅተው በመጫወት ተደጋጋሚ ዕድሎችን ፈጥረው የግቡ አግዳሚ እና ቋሚ በሰፊ ጎል እንዳይመሩ ቢያግዷቸውም በሁለተኛው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ብልጫ ተወስዶባቸው ለማፈግፈግ የተገደዱት ሀዋሳ ከተማዎች በዚህኛውም ጨዋታም ከመስመር ወደ ሳጥን ውስጥ በሚጣሉ ኳሶች ምን ያህል አደገኛ ቡድን መሆናቸውን አስመስክረዋል።

ተከታታይ ሦስተኛ ጨዋታውን ማሸነፍ የቻለው የሙሉጌታ ምህረት ስብስብ በሊጉ በ13 ነጥብ በ5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በከፍተኛ የጨዋታ ፍላጎት የሚጫወቱ ወጣቶችን ከፍተኛ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር ያዋቀሩት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ጨዋታዎች እንደሚፈልጉት ባህርይ አቀራረባቸውን በመቃኘት ውጤታማ ጉዞ እያደረጉ ይገኛሉ።

👉እየረፈደበት የሚገኘው ጅማ አባጅፋር

በርከት ባሉ የሜዳ ውጭ ጉዳዮች አዙሪት ውስጥ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን በሊጉ ሁሉንም የጨዋታ ሳምንት ከተጫወቱ ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን እስካሁን በሦስት ጨዋታዎች ባስመዘገባቸው የአቻ ውጤቶች በሰበሰበው ሦስት ነጥብ እና በአስራ አንድ የግብ እዳዎች በሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል።

እርግጥ ከበላያቸው ከሚገኙ ቡድኖች ያላቸው የነጥብ ልዩነት እጅግ የጠበበ ቢሆንም እንደነ አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ያሉ ቡድኖች በየጨዋታው የመሻሻል ፍንጮችን ብሎም ማደግ የሚችሉ ምልክቶችን ሲያሳዩ በተቃራኒው ጅማ አባ ጅፋር ግን ይህ ነው የሚባል ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ ማሳየት እንደተሳነው ቀጥሏል።

ታድያ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ጊዜ አራፊ በሚሆኑበት በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንትን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የቡድኑ አመራሮች እና አባላት የቡድኑን የውድድር ዘመን ጉዞ ሳይረፍድ ወደ መስመር ለማስገባት ወሳኝ ጊዜ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የአሰልጣኙን ጉዳይ መፍታት እና የቡድኑን ሞራል ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎችን መሥራት በአፋጣኝ ሊሰሩ የኚገቡ ተግባራት መሆንም ይገባቸዋል።

የሊጉ መርሐ ግብር ወደ ጅማ ካመራ ወዲህ እንዳለመታደል ሆኖ ጠንካራዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ ሽንፈትን ያስተናገደው ቡድኑ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የራሳቸው ከሆነው የጅማ ስታዲየም የተሻለ ስፍራ ፈልጎ ማግኘት ከባድ መሆኑን አምኖ በቀሩት የሊጉ የጅማ መርሐ ግብሮች አዎንታዊ ውጤትን ማስመዝገብ ይኖርበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ