ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

የዐበይት ጉዳዮች ሦስተኛ ክፍል ትኩረታችን አሰልጣኞች ላይ አተኩሮ እንዲህ ተሰናድቷል።


👉ያለ ዋና አሰልጣኙ ጨዋታ ያደረገው ጅማ አባጅፋር

የአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በኃላፊነት የመቀጠላቸው ጉዳይ አጠራጣሪ የሆነበት ጅማ አባጅፋር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ በተሸነፈበት ጨዋታ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የመራው ምክትል አሰልጣኙ የሱፍ ዓሊ ነበር።

ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር ባልተከፈለ ደሞዝ እንዲሁም በውጤት መጥፋት መካረር ውስጥ የገቡት የቡድኑ አመራሮች በቀጣይ ከአሰልጣኙ ጋር ያላቸው እና በእንጥልጥል ላይ ያለው ጉዳይ በምን መልኩ እንደሚፈታ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም አሰልጣኙ ከቀናት በፊት ቡድኑን ትተው አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

በቀጣይ ቡድኑ በምክትል አሰልጣኙ እና ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች ቡድን በጊዜያዊነት በመሩት አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ ይቀጥላል ወይንስ ደግም ወደ ሌሎች አሰልጣኞች አይኑን ያማትራል የሚለው ጉዳይ ትኩረትን የሚስብ ነው። እንደሚታወቀው ቡድኑ ከሚገኝበት ወቅታዊ ችግር አንፃር አሰልጣኞች ጅማን ተመራጭ መዳረሻቸው ለማድረግ ፈቀደኛ የመሆናቸው ነገር ቢያጠራጥርም በቀጣይ የክለቡ አመራሮች በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘውን ክለባቸውን ለመታደግ እጅግ ቁልፍ የሚባል ውሳኔ ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል።

👉ቁጥቡ አሰልጣኝ በመጨረሻም በዳኞች ላይ ምሬቱን አሰምቷል

ለሽንፈታቸውም ሆነ በድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው ወቅት ሰበብ ማቅረብን ሆነ ሌሎች አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ከሚቆጠቡ በሊጉ ከሚገኙ ጥቂት አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆኑት የሰበታ ከተማው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን በዳኝነት ዙርያ ጠንከር ያለ ወቀሳን አቅርበዋል።

በእርግጥ የጨዋታውን መልክ ልትቀይር ትችል የነበረችው የፍፁም ገ/ማርያም ጎል መሿራ ከዚህ ቀደም በቡናው ጨዋታ ከተሻረው ግልፅ የጎል ማግባት አጋጣሚ ጋር ተዳምሮ በሁለተኛው አጋማሽ የቡድኑ ተጫዋቾች ስሜታዊ በመሆናቸው ከጨዋታ ቅኝት ወጥተው ግቦችን አስተናግደው የተሸነፉት አሰልጣኙ ዳኞች በቅርበት ሆነው እየተከታተሉ ችላ ስለሚሏቸው ውሳኔዎች ፣ ስለተሻሩባቸው ጎሎች ፣ ዳኞች በውድድሩ ላይ እያሳደሩ ስለሚገኙት አሉታዊ ተፅዕኖ እና ተያያዥ ጉዳዩች ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል።

👉ዘላለም ሽፈራው ዳግም በፕሪምየር ሊጉ ብቅ ብለዋል

ከዚህ ቀደም በተለይ በደቡብ ፖሊስ እና ሲዳማ ቡና በነበረው ቆይታ አስደናቂ ቡድኖች በመገንባት የሚታወቁት ዘላለም ሽፈራው ለተወሰኑ ጊዜያት ከፕሪሚየር ሊጉ አሰልጣኝነት ቢርቅም ወላይታ ድቻን በመረከብ ዳግም ወደ ሊጉ መመለስ ችለዋል።

በ2011 የውድድር ዘመን ደቡብ ፖሊስን ካሰለጠኑ ወዲህ በተሰረዘው የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊግ ይወዳደር የነበረው መከላከያ ሲያሰለጥኑ የነበሩት አሰልጣኙ ያለፉትን ወራት ክለብ አልባ ሆነው ቢያሳልፉም በወላይታ ድቻ የአሰልጣኝ ደለለኝን ስንብት ተከትሎ ወንበሩን ለመረከብ ችለዋል።

አስተቸጋሪ አጀማመርን እያደረገ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እየተመራ የመጀመሪያውን ጨዋታ ቢያደርግም ሽንፈት ከማስተናገድ ግን አልዳነም።

ዓበይት አስተያየቶች

👉ማሂር ዴቪድስ ስለ ፎርሜሽን ምርጫቸው እና አቤል ያለው በአቤል እንዳለ መለወጡ ታክቲካዊ ስለመሆኑ

“4-3-3ንም ሆነ 4-4-2ትን ለመጫወት የተለየ ምርጫ የለኝም፤ እንደሁኔታው ይወሰናል። ጨዋታውን በምንቀርብበት መንገድ እና ተጋጣሚያችን በሚያደርገው ነገር ላይ ይወሰናል። ስለዚህ እንደሁኔታው ተለዋዋጭ መሆን ይኖርብናል። እንደ ሳላሀዲን ፣ ንጋላንዴ እና አቤል ያሉ ተጫዋቾች ገብተው ልዩነት እንዲፈጥሩ ማድረግም ነበረብን።

“ቅያሪው ታክቲካዊ ነበር። የሚያገናኝ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥ ሰብሮ የሚገባ ተጫዋች ያስፈልገን ነበር። ተጋጣሚያችን ከኋላ የሚታይ ባለ አምስት የተከላካይ ክፍል ነበረው። በሦስቱ ተከላካዮች መሀል በጣም ጠባብ ክፍተት ነበር የነበረው። ስለዚህም መሀል ላይ ኳስ ይዞ ወደ ውስጥ የሚገባ ሰው ያስፈልገን ነበር። እንዲህ ዓይነት ተጨዋች ሁሌም የሚገኝ ዓይነት አይደለም። እምብዛም እየተጫወት ያልነበረ ቢሆንም ዛሬ ጥሩ አስተዋፅኦ በማድረጉ ምስጋና ይገባዋል።

👉ዘላለም ሽፈራው ጥንቃቄ ስለመምረጣቸው

” እንደሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለቻምፒዮንነት ከሚጫወቱ ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው። ሁለተኛ መጀመሪያ የራስህን ቡድን ነው የምታየው። የእኛ ስብስብ ከፊት ላይ ትንሽ የመሳሳት ነገር ስላለው ጥንቃቄው ላይ ትኩረት አድርገን በምናገኘው አጋጣሚ የምናስቆጥርበትን መንገድ ነው የመረጥነው። ለዚህም ደግሞ የነደፍነው ስትራቴጂ በተለይ ከመስመር የሚመጡ ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ጥንቃቄ እንድናደርግ ነው የነበረው። መጨረሻ አካባቢ በሰራነው ስህተት ግን ጎል እንዲቆጠርብን ሆኗል።

👉አብርሀም መብራቱ ስለ ፉዐድ ፈረጃ ጉዳት ስለነበረው ተፅዕኖ እና ስለዳኝነት ጉዳዮች

” በትክክል ተፅዕኖ ነበረው። የመሀል ክፍሉን ፈጣሪ በሆኑ ተጫዋቾች ለመገንባት ነበር መጀመሪያ ይዘን የገባነው ፤ ልጁ ተጎድቶ ወጣ። የተጎዳበት ሁኔታ ግልፅ እየሆነ ዳኞች በአምስት ሜትር ርቀት ማየት ካልቻሉ ይሄ በጣም ጉዳት ነው። ከዚያም በኋላ ተደጋጋሚ ጥፋቶች ሲሰሩ ዳኞች ለምን ዝምታን እንደመረጡ ለእኔ ግልፅ አይደለም። ከዛ በተጨማሪ በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ በእኛ በኩል መጠነኛ የአካል ብቃት መውረድ እንዳለ ሆኖ በሥነ-ልቦናም ተጎድተናል። ከዚህ በፊትም ያገባናቸው ኳሶች ናቸው የሚሻሩት አሁንም የምናገባቸው ኳሶች ይሻራሉ ፣ ዳኞች በውድድሩ ላይ ትንሽ ተፅዕኖ እያደረጉ ነው ፤ ለውጥ እያመጡ ነው። እና ያ የተጨዋቾቼን ስሜት ጎድቶታል። ተጫዋቾቼም ስሜታዊ ከሆኑ በኋላ ከዳኞች ጋር በነበራቸው ምልልስ በተለይም ከረዳር ዳኛው ጋር ያሬድ በቀይ ወጥቷል። ግን ጨዋታው በምንፈልገው መልኩ ሊሄድ አልቻለም። ስለዚህ በዚህ በኩል ስለዳኝነቱ ብዙ ማለት ባልችልም። ዳኞች የውድድሩ ህይወቶች ናቸው ስህተትም ሊሰሩ ይችላሉ። ግን እንዲህ ዓይነት ቀላል እና የወረደ ስህተት መስራት ግን በዚህ ትልቅ ሊግ ላይ አይጠበቅባቸውም ማለት እፈልጋለሁ።

👉ፋሲል ተካልኝ ፍፁም ዓለሙ ቡድኑ ወደ ጨዋታው እንዲመለስ ስለማስቻሉ

አሁን እኔ ስለ ቡድኔ ባወራ ይሻላል። ፍፁም ሁሉም ሰው የሚያውቀው ነው። ጥሩ ተጫዋች ፣ ልዩነት ፈጣሪ መሆኑን ሁሉም ሰው ያውቀዋል። ዛሬ ግን እንደቡድን ከሽንፈት ወጥተን በጥሩ ጨዋታ ወደ አሸናፊነት መግባታችን ለእኛ ብዙ ነገር ማለት ነው። በዕረፍትም የነገርኳቸው በየቀኑ ነጥቦችን መጣል እና መሸነፍ ለእኔም ለእነሱም ክብር እንደማይመጥን ነበር የነገርኳቸው። ግን በመጨረሻ ተሳክቷል እና ደስ ብሎኛል።

👉 ዘርዓይ ሙሉ ስለ ሀዋሳው ጨዋታ እና ስለዳኝነት

ጨዋታው ሁለት ዓይነት መልክ ነበረው። መጀመርያ ልንጫወት ያሰብነውን እነሱ ተጫወቱ። ከዕረፍት በፊት ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል። በዛም ጎል አስቆጠሩ። ከዛ በኋላ ኳሱን ለመቆጣጠር ተጫዋቾች ቀይረን ሞክረን። ከዕረፍት በኋላም በልጠን ተጫውተን ነበር። እውነት ለመናገር ዳኞች በሚሰሩት ስህተት ዋጋ ከፍለናል። ሞክንያቱም እዚህ ጥፋት ሲሰራ እና በእጅ ሲነካ በዝምታ እየታለፈ ነበር። ቢያንስ አቻ የመሆን ዕድል ነበረን። ይህ ጉዳይ በትኩረት ሊታይ ይገባል።

👉ካሳዬ አራጌ በቡድኑ ውስጥ ስላለው ጉጉት

በቡድን ውስጥ ያለው ጉጉት ተነሳሽነት ይፈጥራል። ግን የምንፈልገውን ነገር እስከሚያጠፋ ድረስ መሄድ የለበትም። ጨዋታውን ለማሸነፍ እና የማሸነፍ ጉዟችንን አስጠብቆ ለመሄድ ያለው የመጓጓቱ ስሜት ነገሮችን እንዳናስተውል ያደርገናል። ይህንን ማረም አለብን። ይህንን ብልም ግን ፍላጎቱ እና ጉጉቱ ያስፈልጋል። ምክንያቱም በጎ ጎን ስላለው።

👉ሥዩም ከበደ ስለናትናኤል ገብረጊዮርጊስ የዕለቱ ብቃት

ናቲ የሚገርምህ ነገር እኔ ከፋሲል ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ የምታይበት ነገር በጣም ያጓጓል ፤ በተለይ ልምምድ ላይ። እንደውም አሁን እዚህ 10% የሰራው ነገር የለም። ልምምድ ላይ ጉልበቱ ፣ አቅሙ የሚያደርጋቸው ነገሮች ልክ እንደበሳል ተጫዋች ነው እንቅስቃሴ የሚያደርገው። እንደዚህ ዓይነት ተጫዋቾች የሚያስፈልጋቸው የጨዋታ ልምድ ብቻ ነው። ስለዚህ ፋሲል ላይ በአንድ ጊዜ ወጣቶቹኑ እያስገባህ ትልቅ ይሆናሉ ማለት አይደለም። ግን እንዲህ ዓይነት ክፍተት እየሰጠሀቸው እንዲጠቀሙ ማድረግ ከዛ ልጁ ራሱ እያዳበረ የሚሄደው በራስ መተማመን አለ። ከሲኒየሮች ያላነሰ ብዙ ነገር የማድረግ አቅም አለው። ስለዚህ በዚህ መልኩ ከመጣ ለፋሲል ብዙ ዓመት የሚያገለግል ለሀገርም የሚያገለግል ጠንካራ ተጫዋች ይሆናል ብዬ አስባለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ