ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የስምንተኛ ሳምንት ሌሎች ዐበይት ጉዳዮችን እነሆ! 


👉በተጋጣሚ ሜዳ አፈትላኪ ሩጫዎችን ማድረግ ፈተና የሆነባቸው አጥቂዎች

በዘመናዊ እግር ኳስ ቡድኖች ከፊት ጫና ፈጥረው ለመጫወት ይረዳቸው ዘንድ በተጫዋቾቻቸው መካከል በሜዳው ቁመት የሚኖረውን ርቀት ለማጥበብ ይረዳ ዘንዳ የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሐል ሜዳ አስጠግተው መጫወት የተለመደ ነው።

ታድያ ይህ “ከፍተኛ ስጋት ፣ ከፍተኛ ውጤት” ያለው አጨዋወት በሀገራችን ቡድኖች ምንም እንኳን አተገባበር ላይ ሰፊ ክፍተቶች ይኖሩት እንጂ በስፋት ለመተግበር ሙከራዎች ሲደረጉ ይስተዋላል፡፡ ታድያ በመሰል መንገድ ከሚቀርቡ ቡድኖች በተቃራኒ የሚገቡ ቡድኖች ተጫዋቾች በተለይም አጥቂዎች ተጋጣሚያቸው የተከላካይ መስመሩን ወደ ፊት በማስጠጋቱ በግብ ጠባቂው እና በመከላከል መስመሩ መካከል የሚገኘውን ክፍተት (ጥልቀት) ጊዜያቸውን የጠበቁ አፈትላኪ ሩጫዎችን በማድረግ ለመጠቀም ጥረት ማድረጋቸው የተለመደ ነው።

ነገር ግን በሀገራችን በዚህ ሂደት አፈትልከው የሚወጡ አጥቂዎች በአመዛኙ ‘ከጨዋታ ውጪ ናችሁ’ በሚል በተደጋጋሚ የጨዋታ ሂደቶች ሲቋረጡ ይስተዋላል፡፡ ለዚህም የተጫዋቾች የጊዜ አጠባበቅ እና አስተካክሎ አቋቋምን አዘጋጅቶ የመጠበቅ ክፍተቶች እንዳሉ ሆኖ በዳግም ምልሰት ሲታዩ በጨዋታ ውስጥ የነበሩ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በሚል መያዛቸው በዳኝነቱ ላይ ያሉ ክፍተቶች ማሳያ ናቸው።

በዚህም መነሻነት በሀገራችን የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሀል የሚያስጠጉ ቡድኖች በዳኝነቱ “በስውር” እያገኙ የሚገኙት ጥቅም እስኪመስል ድረስ መሰል ሂደቶች በተደጋጋሚ እየተስዋሉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ለተጋጣሚ አጥቂዎች ሁኔታዎችን ፈታኝ ሲያደርግ ለሚከላከለው ቡድን ደግሞ “በስውር” ጥቅሞችን እያስገኘ ይገኛል።

👉የኢትዮጵያ ቡና እና ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጉዳይ

ኢትዮጵያ ቡና በቅርቡ የክለቡን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር ይረዳው ዘንድ ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር በየዓመቱ የሚታደስ በዓመት አምስት ሚልየን ብር የሚያስገኝለትን የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ማድረጉ ይተወሳል።

ስምምነቱን አስመልክቶ በፅሁፍ በወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በግልፅ “በስምምነቱ መሰረት ክለቡ የባንኩን አርማ በተጫዋቾች ቲሸርትና ቁምጣ ላይ በማሳየት ባንኩን ያስተዋውቃል፡፡በተጨማሪም በሜዳውም ይሁን ያለ ሜዳው ጨዋታ በሚኖረው ወቅት የባንኩ ቢልቦርድ ማስታወቂያ በጨዋታው ሜዳ አካባቢ እንዲቀመጥ ያደርጋል። ክለቡ በተቻለው መጠን የባንኩን ብራንድ እና አገልግሎቶች እንዲያስተዋውቅም በስምምነቱ ተካትቷል።” የሚል ሀሳብ ይገኝበታል።

በስምምነቱ መሰረት ከጥቂት የጨዋታ ሳምንታት አስቀድሞ ቡድኑ ጨዋታ በሚያደርግባቸው ወቅት የባንኩ የማስታወቂያ ቦርዶች በሜዳው ጠርዝ መታየት የጀመሩ ሲሆን በማልያው እና ቁምጣ ላይ ግን የታሰቡት የባንኩ አርማዎች እስከዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድረስ ተፈፃሚ መሆን ሳይችሉ ቀርተው ነበር።

በዚህ ፅሁፋችን የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ መለያ (ሎጎ) በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ቡና መለያ መታየት ከመጀመሩ ጋር አንድ ልብ ያልተባለ ጉዳይን ለማንሳት ወደድን።

በዓለማችን እግር ኳስ የማሊያ ላይ ማስታወቂያዎች እጅግ የተለመዱ ናቸው። በዋነኝነት እነዚህ ማስታወቂያዎች በማሊያው የፊተኛው ገፅ በመሀከለኛው ክፍል እንዲሁም የቀኝ የላይኛው ክፍል ላይ የተለመዱ ሲሆን በተጨማሪነትም በስተጀርባ ባለው የማሊያው ገፅ ደግሞ ከተጫዋቾች ቁጥር በላይ ወይንም በታችኛው ክፍል አለፍ ሲል ደግሞ በሁለቱ እጀታዎች እንዲሁም ቁምጣዎች ላይ እንደየአስፈላጊነቱ ሲደረጉ ይስተዋላል። እነዚህም በመለያው ላይ የሚገኙ ቦታዎች የተመረጡበት ምክንያት ለዕይታ የተመቹ መሆናቸው ቀዳሚው መመዘኛ ነው።

ታድያ እንደ ሀገራችን ከተለመደው የስፖንሰር ሺፕ ትርጓሜ ማለትም የእርጥባን አስተሳሰብ (ዕርዳታ) ከሚለው ወጥተን በዓለምአቀፍ ዐውድ ስንተረጉመው ዋነኛው መርሁ ሰጥቶ መቀበል ነው። በዚህም ግለቦች ለሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ በምላሹ የሚጠበቅባቸው አንዳች ነገር አለ፡፡ ይህም የተቋሙን ገፅታ ለመገንባት የሚረዳ ዕይታ (visibility) መፍጠር ነው። ይህም የስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ተቀዳሚ የትኩረት ነጥብ መሆኑ ግልፅ ነው ፤ ታድያ የኢትዮጵያ ቡና መለያ ላይ የታተመው የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ መለያ (ሎጎ) በኢትዮጵያ ቡና መለያ ላይ ያረፈበት ስፍራ ለዕይታ እጅግ አስቸጋሪ በሆነው እና የመለያው የቀኝ እጀታ ክፍል ወደ ውስጠኛው የእጀታው አካባቢ ያደላ ነው።

በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ቡና እየተጠቀመበት የሚገኘው የሜዳ ውስጥ ተጫዋቾች መለያ ንድፍ (Design) መሰል ማስታወቂያዎችን ታሳቢ አለማድረጉ እንዳለ ሆኖ ክለቡ የባንኩን መለያ (ሎጎ) በመለያው ላይ የተቀመጠበት ቦታ ግን ከዕይታ አንፃር አዳጋች ከመሆኑ አንፃር ሊታሰብበት ይገባል ፤ ይህም ከሰጥቶ መቀበል መርህ አንፃር ተቋማት በጋራ የመስራት ፍላጎት አሳይተው ሲመጡ ተጠቃሚነታቸውን በማጉላት ይበልጥ የክለቡን ብራንድ ለሌሎች ስፖንሰር አድራጊዎች ሳቢ ከማድረግ አንፃር ተግዳሮት ሊፈጥር ስለሚችል በፍጥነት ማስተካከል ይገባል።

👉በማሊያ ላይ የሚሰፍሩ ፅሁፎች

የሀገራችን ክለቦች እና የመለያ ጉዳይ ብዙ ሊባልበት የሚችል ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል ፤ ለማሳያነትም አሁን አሁን ለውጦችን እየተመለከትን እንገኛለን እንጂ ክለቦች ለሜዳ ውስጥ ተጫዋቾች መለያ ከሚሰጡት ትኩረት አንፃር ለግብ ጠባቂዎች መለያ እምብዛም ትኩረት ሲሰጡ አይስተዋልም።

ለአብነት በሊጉ ከሚካፈሉ ክለቦች ገሚሱን ያክል የሚሆኑት ግብ ጠባቂዎች የክለቡ አርማ ያላረፈበት መለያዎችን ሲጠቀሙ መስተዋላቸው የዚህ ጉልህ ክፍተት በማሳያነት መቅረብ የሚችል ጉዳይ ነው:: ታድያ ለዚህኛው ነጥባችን መነሻ የሆነን የጅማ አባ ጅፋሩ ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዜ መለያ በጀርባው የሰፈረው የእንግሊዘኛ “M” ፊደል ጉዳይ ነው።

ይህ በጉልህ በሚታይ መልኩ የተፃፈው የእንግሊዝኛ ፊደል ትርጉም ወይንም መልዕክት ምንም ይሁን ምን የተጫዋቹ ስም ፣ የትጥቅ አምራቹ ኩባንያ መጠርያ አልያም የክለቡ አጋር ባልሆነበት ሁኔታ በጉልህ ተፅፎ እስካሁን በሊጉ ግብ ጠባቂው በሚጠቀምባቸው መለያዎች ላይ ሰፍሮ መገኘቱ አስገራሚ ያደርገዋል።

አወዳዳሪው አካልም ተጫዋቾች በጨዋታ ዕለት የሚጠቀሟቸውን መለያዎችን ሆነ ሌሎች አልባሳትን በደንብ የመመርመር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

👉አሁንም በቂ ትኩረት ያልተሰጠው የጨዋታ በፊት የሜዳ ዝግጅት

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ካደረጉት ጨዋታ መጀመር ሠላሳ ያህል ደቂቃዎች እስኪቀሩት ድረስ በስታድየሙ በሚገኙት ግቦች ላይ መረብ ስላለመሰቀሉ አንስተን ነበር ፤ ታድያ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም ደግሞ ሌላ የጥድፊያ ስራ ተመልክተናል። የሳምንቱ መክፈቻ ጨዋታ ከነበረው የሰበታ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ መጀመር ጥቂት ደቂቃዎች እስኪቀሩ ድረስ በሜዳው ላይ የሚገኙት መስመሮች በደማቁ አለመሰመራቸው ሌላው የታዘብነው ጉዳይ ነው።

እርግጥ ነው በጨዋታ ሳምንታት መካከል ያለው የቀናት ልዩነት አጭር መሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀሬ ቢሆንም መሰል ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን በአግባቡ በተቀመጠላቸው ጊዜያት መከናወን የሚገባቸው ጉዳዮች ግን ችላ ሊባሉ አይገባም።

👉አሽከርካሪ ማሰልጠኛ መኪና ስታዲየም የደረሱት ጅማ አባ ጅፋሮች

በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታድየም ጅማ አባጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና ካደረጉት የ8ኛ ሳምንት የማሳረጊያ ጨዋታ መጀመር በፊት አንድ እንግዳ የሆነ ክስተትን ተመልክተናል።

ለወትሮው ክለቦች ከጨዋታው መጀመር በፊት ከተዘጋጀላቸው ማረፊያ ውድድሩ ወደ ሚደረግበት ስታድየም በክለቡ አውቶብስ ይጓዛሉ ፤ በዚህኛው ጨዋታ ቀን ግን የተመለከትነው ሌላ ነው።

ጅማ አባ ጅፋሮች ወደ ስታድየም በክለቡ የመጓጓዣ አውቶብስ ከመምጣት ይልቅ ንብረትነቱ የአንድ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋም በሆነ የመለማመጃ “የቅጥቅጥ አውቶብስ” ወደ ስታድየሙ የመጡበት ሂደት እጅግ አስገራሚ ነበር።

አይደለም እና ለእግር ኳስ ተጫዋቾች ለሌላውም ህብረተሰብ በተጠባባቀ የወንበር አደራደር ምቾት የማይሰጡትን እነዚህን አውቶብሶች ጥቅም ላይ ማዋሉ የክለቡ ደካማ የሜዳ ውጪ አካሄድ የት ድረስ እንደደረሰ ጥሩ ማሳያ ነው። የክለቡ አውቶብስ ድንገተኛ የቴክኒክ ችግር ቢገጥመው እንኳን ዩኒቨርስቲውን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ ሌሎች ተቋማት ክፍተቱን መሸፈን ያቅታቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከሁሉም በላይ ተጫዋቾች ከመኪና ወርደው ወደ ስታድየም ሲገቡ በሱፐር ስፖርት ካሜራዎች እይታ ውስጥ በመሆናቸው ጉዳዩ የሊጉንም ገፅታ ጭምር የሚነካ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

👉የመጫወቻ ሜዳ የአርማታ ጠርዝ ጉዳይ

በኦሊምፒክ ስታዲየም ስታንዳርድ የተገነባው የጅማ ስታዲየም የመጫወቻ ሳሩን ከጊዜያዊ ትራክ የሚለየው እና በመጫወቻ ሜዳው ሳር ዙርያ የተሰራው የአርማታ ጠርዝ ጉዳይ ልብ ሊባል የሚገባ መሆኑን አስተውለናል።

ሀዋሳ ከተማን ከሲዳማ ቡና ባገናኘው ጨዋታ በአንድ የጨዋታ ቅፅበት የሀዋሳው የግራ የመስመር ተከላካይ ደስታ ዮሐንስ በሜዳው ጠርዝ ጥፋት ተሰርቶበት በወደቀበት ወቅት ይህ የአርማታ ስሪት ጠርዝ ለጥቂት ሳያገኘው ቀረ እንጂ ተጫዋቹ እጅግ አደገኛ ጉዳት ሊያስተናግድ በቻለ ነበር። ያልታሰበ ችግር ተፈጥሮ ፀፀት ውስጥ ከመውደቅ በፊትም አወዳዳሪው አካል የስታድየሞችን ምቹነት እና ደህነትን ሲያረጋግጥ መሰል በጉዳዮችንም ማጤን ይገባዋል፡፡ በዚህም በማስታወቂያ ቦርድ ባልተከለለው የሜዳው ክፍል አካባቢ ይህን የአርማታ ጠርዝ ጉዳት በማያስከትል መልኩ ሊሸፈን የሚችልበት መንገድ ቢታሰብ መልካም ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ