ሪፖርት | የጦና ንቦቹ እና የጣና ሞገዶቹ ነጥብ ተጋርተዋል

የ12ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ የሆነው የወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል።

የ11ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አራፊ ቡድን የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በ10ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ጅማን ሲረቱ ከተጠቀሙት ቋሚ 11 ነጋሽ ታደሰ እና መልካሙ ቦጋለን በእንድሪስ ሰዒድ እና ቸርነት ጉግሳ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል። በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት ባህር ዳሮች በበኩላቸው ከጅማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቀዳሚ የተጫዋቾች ስብስብ ሦስት ተጫዋቾችን ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድን በሀሪሰን ሄሱ፣ ሳሙኤል ተስፋዬን በሚኪያስ ግርማ እንዲሁም በረከት ጥጋቡን በፍቅረሚካኤል ዓለሙ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

የካቲት 12 ታስቦ የሚውለውን የሰማዕታት ቀን ለአንድ ደቂቃ በማሰብ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በፈጣን እንቅስቃሴዎች ታጅቦ ቢጀመርም ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ግን መቀዛቀዞች ተስተውሎበታል። በተለይ የጣና ሞገዶቹ ፈጣኖቹን ከወገብ በላይ ያሉ ተጫዋቾች በመጠቀም የጨዋታውን የመጀመሪያ ደቂቃዎች ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በተቃራኒው ከኳስ ውጪ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያሳለፉት የጦና ንቦቹ ተሻጋሪ እና የመልሶ ማጥቃት ኳሶች ላይ ትኩረት በመስጠት ጨዋታውን ቀጥለዋል።

በመቀመጫ ከተማቸው ጨዋታውን ያደረጉት ባህር ዳሮች ኳስን ተቆጣጥረው ቢጫወቱም ግጥግጥ ብሎ የነበረውን የወላይታ ድቻ የመከላከል አደረጃጀት ማስከፈት ሳይችሉ ጨዋታው ቀጥሏል። ቡድኑ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራም በ24ኛው ደቂቃ በአፈወርቅ ኃይሉ አማካኝነት አድርገው መክብብ ደገፉ አምክኖባቸዋል። በራሳቸው የሜዳ ክልል ላይ ጨዋታውን ቀጥለው በ40ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቅጣት ምት ወዲያው የጀመሩት ድቻዎች በፀጋዬ ብርሃኑ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ጥረው የባህር ዳሩ የመሐል ተከላካይ መናፍ ዐወል በሚገርም ቅልጥፍና ኳሱን አምክኖታል። የጨዋታው አጋማሽም ግብ ሳይስተናገድበት 0-0 ተጠናቋል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ፍጥነት የታከለበት እንቅስቃሴ ያስመለከቱት ባህር ዳሮች በጨዋታው ቀዳሚ ለመሆን ጥረቶችን በመስመር ላይ መሰንዘር ይዘዋል። በተለይም ግርማ ዲሳሳን ቀይሮ በማስገባት እና በጨዋታው በበረከት ወልዴ ተይዞ የነበረውን ፍፁም ዓለሙን ወደ መስመር ተጠግቶ የወሰኑ አጋዥ እንዲሆን በማድረግ የዲቻዎችን ጥቅጥቅ ያለ የተከላካይ ክፍል እንዲዘረዘር ሞክረዋል። ባህር ዳሮች ይህንን ጥረት ቢያደርጉም ጠንካራውን የድቻ የተከላካይ ክፍል መስበር አልቻሉም።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሩብ ሰዓታት ሲቀሩትም አህመድ ረሺድ በግራ መስመር ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ፍፁም ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ መክኖበታል። በደቂቃዎች ልዩነትም ወላይታ ድቻዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ጥቃት ሰንዝረው ነበር። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም በ85ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል ያመሩት ዲቻዎች በቸርነት ጉግሳ አማካኝነት እጅግ ለግብነት የቀረበ ሙከራ አድርገው ሀሪስተን ሄሱ አምክኖባቸዋል።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃው በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው በረከት ወልዴ ፍፁም ዓለሙ ላይ በሰራው ጥፋት ባህር ዳሮች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ጥፋቱን የሰራው በረከት ወልዴም በዕለቱ ዳኛ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከጨዋታው እንዲሰናበት ሆኗል። የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ባዬ ገዛኸኝ ቢመታውም ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በጥሩ ብቃት አምክኖበታል። ጨዋታውም ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በአሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመሩት ወላይታ ድቻዎች 11 ጨዋታዎችን አድርገው በሰበሰቡት 11 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ አራተኛ ተከታታይ አቻቸውን ያስመዘገቡት ባህር ዳሮች ደግሞ በ12 ጨዋታ በሰበሰቡት 17 ነጥብ ያሉበት 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ