ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የጨዋታ ሳምንቱን ሁለተኛ ቀን ሁለተኛ ግጥሚያ የተመለከተው ዳሰሳችን እንዲህ ይነበባል።

በሁለቱ የሰንጠረዡ ክፍሎች ባሉ ፉክክሮች ውስጥ የሚገናኙት ድቻ እና ቡና ከዚህ ጨዋታ የሚያገኟቸው ነጥቦች ከቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው ጋር ባላቸው ልዩነቶች ውስጥ ለውጥን መፍጠር ይችላሉ።

በቅዱስ ጊዮርጊስ የዓመቱን ስድስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ ከአደጋው ክልል በሁለት ደረጃዎች ለመራቅ የሚያስችሉ ነጥቦችን ፍለጋ ከቡና ጋር ይፋለማል። ነጥብ በተጋራበት የሰበታ ከተማው ጨዋታ እንደሰጠው ፍንጭ ሁሉ ከጊዮርጊስ ጋርም ጥብቅ መከላከልን ምርጫው አድርጎ የቀረበው ቡድኑ በመጨረሻ የሰራው ስህተት አንድ ነጥብ እንዳያገኝ አደርገችው እንጂ ለሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ መረቡን ሳያስደፍር ለመውጣት ሰባት ደቂቃዎች ብቻ ቀርተውት ነበር።

ነገም በተመሳሳይ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አብዛኛውን ደቂቃ የመስመር ተመላላሾቻቸውን ጨምሮ አምስት የኃላ ክፍል ተሰላፊዎችን በመጠቀም የሜዳውን ስፋት ለቡና መጠቀሚያነት እንዳይውል እንደሚዘጉ ይጠበቃል። ወደ ራሱ ሜዳ ቀርበው ቅብብሎችን የሚከውኑ የተጋጣሚው አማካዮችንም ተመጣጣኝ ቁጥር ባላቸው የመሀል ክፍል ተሰላፊዎቹ ለመቆጣጠር መጣሩ የሚቀር ጉዳይ አይሆንም። ለታዳጊው ቢኒያም ፍቅሬ የመጀመሪያ ዕድል ለመስጠት ያስገደደው የአጥቂ መመስር ክፍተቱ ግን የቡና የኃላ ክፍል ድክመትን በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት ግብ ላይ ለመድረስ እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል። ያም ቢሆን እንደ ፀጋዬ ብርሀኑ ያሉ ተጫዋቾቹ ታታሪነት የቡናን የኋላ ክፍል ጫና ውስጥ የመክተት አቅም ሊኖረው ይችላል። ሁኔታዎች ተሳክተው ድቻ አንድ ጎል ካገኘ ግን የቡድኑ የመከላከል አጥር ይበልጥ መጠናከሩ እና በሙሉ ኃይል ማፈግፈጉ የግድ ይሆናል።

ሦስት ተከታታይ ድሎችን ያሳኩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀድሟቸው ጨዋታውን የሚያከናውነው ፋሲል ከነማ ጋር መሳ ለመሳ ለመሆን ከድቻ ሦስት ነጥቦችን ይፈልጋሉ። ይህንን ለማድረግ ግን በሸገር ደርቢው ሁለተኛ አጋማሽ እና በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ ከገጠማቸው የመከላከል አጥር በላይ ከፍ ያለ ፈተና ይጠብቃቸዋል። በተጋጣሚ ሜዳ ክፍተት ፍለጋ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት መቆየትን እየተላመደ የመጣው አማካይ ክፍላቸው እና በጥሩ ሁኔታ በማጥቃት ሂደቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉት የመስመር ተከላካዮቻቸው የሰሞኑ ትጋት ነገም በሜዳው ስፋትም ሆነ ቁመት የተጠጋጋ አቋቋም በሚኖረው ተጋጣሚያቸው ፊት በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል።

ቡና ከተከላካይ ጀርባ ክፍተት በሚያገኝባቸው ቅፅበቶች ያለውን አደገኝነት ለመናገር የአቡበከር ናስር ፍጥነት ላይ የተመሰረቱ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶቹ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያመጡትን ለውጥ ማየት በቂ ነው። ለግቡ እጅግ የተጠጋ ባለሦስት የመሀል ተከላካዮች ጥምረት ጋርስ በምንም መልኩ ክፈተቶችን ያገኛል የሚለው ጥያቄ ከወዲሁ ተጠባቂ ይሆናል። ተለዋዋጭነት በማታይበት አቀራረቡ የተከላካይ መስመሩን መሀል ሜዳው ድረስ በማምጣት በዋነኝነት በዊሊያም እና ታፈሰ አቀናባሪነት በቅብብሎች ላይ ተመስርቶ የተጋጣሚውን በር እንደሚያንኳካ የሚጠበቀው የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡድን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከኃላ ሊተወው የሚችለው ክፍተት ነገ ሰፍቶ ሊታይ ይችላል። እንደጅማው ጨዋታ እዚህ ቦታ ላይ ስህተቶችን ከሰራ ግን ግብ ላለማስተናገዱ ምንም ዋስትና አይኖረውም። እስካሁን ግብ ሳያስተናግድ መውጣት እንዳልቻለ ቡድንም ከተጋጣሚው በላይ ማስቆጠር መቻል ውጤታማ ሲያደርገው ቢቆይም በነገው ጨዋታ እንዳለፉት ቀናት ሦስት ግቦችን ማግኘት ሊከብደው ይችላል።

በጨዋታው ወላይታ ድቻ አሁንም ስንታየሁ መንግሥቱ እና እዮብ ዓለማየሁ ያላገገሙለት ሲሆን በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ተቀይሮ ወጥቶ የነበረው አበበ ጥላሁንን ጨምሮ ቀሪው የቡድኑ ስብስብ ሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ሰምተናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ12 ጊዜያት ተገናኝተው ሦስት ሦስት ጊዜ ሲሸናነፉ በስድስቱ ግንኙነት አቻ ተለያይተዋል። ቡና 10 ፣ ድቻ 8 አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (3-5-2)

መክብብ ደገፉ

አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – መልካሙ ቦጋለ

አናጋው ባደግ – እንድሪስ ሰዒድ – በረከት ወልዴ – ኤልያስ አህመድ – ያሬድ ዳዊት

ፀጋዬ አበራ – ፀጋዬ ብርሀኑ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማሪያም ሻንቆ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አሥራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊሊያም ሰለሞን

አቤል ከበደ – አቡበከር ናስር – ሀብታሙ ታደሰ


© ሶከር ኢትዮጵያ