ሪፖርት | ድሬዳዋ ከጨዋታ ብልጫ ጋር አዳማን ረትቷል

ተከታታይ ሽንፈቶች ገጥመውት የነበረው ድሬዳዋ ከተማ እጅግ ተሻሽሎ በቀረበበት ጨዋታ አዳማ ከተማን 3-0 ማሸነፍ ችሏል።

አዳማ ከተማ በዳንኤል ተሾመ እና ታፈሰ ሰርካ ጉዳት መነሻነት ለማድረግ ከተገደዳቸው ለውጦችን ጨምሮ ኢብሳ አበበ ፣ ብሩክ ቦጋለ ፣ በላይ ዓባይነህ ፣ ዘሪሁን ብርሀኑ እና አብዲሳ ጀማል ወደ ሜዳ ሲያስገባ ሙጃይድ መሀመድ ፣ ፍሰሀ ቶማስ እና ጀሚል ያዕቆብም ሌሎች ከአሰላለፍ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው። በድሬዳዋ በኩል ደግሞ አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን ሦስት ቅያሪዎችን ሲያደርጉ ፍቃዱ ወርቁ ፣ ሱራፌል ጌታቸው እና እንዳለ ከበደ ገብተው ኤልያስ ማሞ፣ ኩዌኩ አንዶህ እና አስጨናቂ ሉቃስ ወጥተዋል።

ጨዋታው ከተጀመረበት ደቂቃ ጀምሮ ከባባድ ጥቃቶችን መክፈት የጀመሩት ድሬዳዋዎች በሙኸዲን ሙሳ እና ጁኒያስ ናንጄቤ አማካይነት ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርገዋል። በቀዳሚዎቹ አምስት ደቂቃዎች ብቻ ሙኸዲን ከግብ አፋፍ ላይ የሳታት እና ጁኒያስ በግቡ ቋሚ የተመለሰበት ኳስ አስደንጋጭ ነበሩ። ከፍተኛ ጫና ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት ድሬዎች ወደ ቀኝ ባደላ ማጥቃት አዳማን አቅም አሳጥተው በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረሳቸው በቶሎ መሪ አድርጋቸውል። 13ኛው ደቂቃ ላይ ናንጄቤ በኢብሳ አበበ አናት ላይ ልኮት ወደ ውጪ ከወጣበት ኳስ ሁለት ደቂቃዎች በኃላ ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ በሙኸዲን ሙሳ ድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት ተቀይሯል።

አዳማ ከተማዎች በተጋጣሚያቸው አስገራሚ አጀማመር መረጋጋት ተስኗቸው ከቆዩ በኋላ ወደግብ የደረሱት 18ኛው ደቂቃ ላይ አዳነ ነላይነህ ከሳጥን ውስጥ አክርሮ በመታው እና በ24ኛው ደቂቃ በትዕግስቱ አበራ የግንባር ኳስ ነበር። ሆኖም ትዕግስቱ ከሙከራው በኃላ ወደራሱ የግብ ክልል ሲመለስ ሙኸዲን ሙሳ በረጅሙ የተላከለትን ረጅም ኳስ በፈጣን ሩጫው ይዞ በመግባት ግብ ጠባቂውንም ጭምር አልፎ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። በቀጣይ ደቂቃዎች መሀል ተከላካያቸውን ፍቃዱ ደነቀን በጉዳት ያጡት ድሬዳዋዎች እንደመጀመሪያው ወደግብ የሚደርሱበት አጋጣሚ ይቀንስ እንጂ በሙሉ ብልጫ አጋማሹን ማጠናቀቅ ችለዋል። ከዕረፍት በፊት እዮብ ማቲያስ የእንዳለ ከበደን ኳስ ከግብ መስመር ላይ ማውጣት ባይችል ኖሮም መሪነታቸው ወደ ሦስት ከፍ ባለ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር 48ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የመጣውን ኳስ አዳማዎች በአግባቡ መውጣት ሳይችሉ ቀርተው አስቻለው ግርማ ከናንጄቤ የተቀበለውን ኳስ ሦስተኛ ግብ አድርጎታል። ራሳቸውን አረጋግተው ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሞከሩት አዳማ ከተማዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ በበቃሉ ገነነ ከሳጥን ውጪ ጠንካራ ሙከራ አርገው ሲወጣባቸው 62ኛው ደቂቃ ላይ የኃላሸት ፍቃዱ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ፍሬው ጌታሁን አውጥቶበታል። ድሬዳዋዎችም እንደመጀመሪያው ሁሉ የጁኒያስ ናጄቤን ፍጥነት በመጠቀም ከተከላካይ ጀርባ ያለውን ሰፊ ክፍተት ለመጠቀም ደጋግመው ወደፊት መሄዳቸው አልቀረም።

አዳማዎች ድፍረት ጨምረው ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል በደረሱባቸው አጋጣሚዎች በበላይ አባይነህ እና አብዲሳ ጀማል የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ደካማ አጨራረስ በማሰየታቸው ልዩነቱን ማጥበብ አልአልቻሉም። የተሻለ በነበረው የቡድኑ ሙከራም በቃሉ ገነነ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል። በጁኒያስ ናንጄቤ በመጨረሻ ደቂቃ ከርቀት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት ድሬዎች ግን ጨዋታውን ከእጃቸው ሳያስወጡ እስከመጨረሻው ዘልቀዋል። በርካታ የግብ ሙከራዎችን ያስመለከተን ጨዋታም በብርቱካናማዎቹ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ