ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በዚህ ሳምንት ትኩረት ያገኙ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዐበይት አስተያየቶችን ቃኝተናል።

👉በመጀመሪያ አጋማሽ የሚደረጉ አስገዳጅ ያልሆኑ ቅያሬዎች

በእግር ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ አስገዳጅ የሆነ የተጫዋቾች ጉዳት እስካልተከሰተ ድረስ አሰልጣኞች የቡድናቸውን ተጫዋቾች ለመቀየር ሲደፍሩ ብዙም አይስተዋልም። በሁለተኛው አጋማሽ ከ60 እና 70ኛው ደቂቃ ወዲህ በተለምዶ የአሰልጣኞች በብዛት ተጫዋቾችን ለመቀየር የሚመርጡት ጊዜም ስለመሆኑ ይስተዋላል።

ታድያ ባልተለመደ መልኩ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያለ አስገዳጅ ምክንያቶች አሰልጣኞች በመጀመሪያ አጋማሽ ተጫዋቾችን ሲቀይሩ እየተመለከትን እንገኛለን። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ በሀዋሳ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ አማካዩ ያስር ሙገርዋን አስወጥተው በምትኩ ዮሴፍ ዮሐንስን ሲያስገቡ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ኤልያስ አህመድን አስወጥተው እንድሪስ ሰዒድን ማስገባት ችለዋል።

ከእነዚህ ቅያሬዎች ጀርባ አሰልጣኞቻችን በቀደሙት ጊዜያት በስፋት ይሰነዘርባቸው የነበረው ለውሳኔዎች የመዘግየት አሉታዊ አስተሳሰብን በመስበር የቡድናቸውን ሆነ የተጋጣሚያቸው እንቅስቃሴ በፍጥነት በመረዳት መሰል ድፍረት የተሞላባቸውን ፈጠን ያሉ የማስተካከያ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ተነሳሽነት ማሳየታቸው እንደ በጎ ጅምር የሚወሰድ ነው።

👉 የፍስሐ ጥዑመልሳን “ከማጥ መውጣት”

እርግጥ ነው የጫናው መጠን ይለያይ እንጂ ሁሉም የእግርኳስ አሰልጣኞች በየራሳቸው መለኪያ እና ቅድመ ግምቶች አንፃር በጫና ውስጥ ይገኛሉ። ውጤት በሚጠፋበት ወቅት በአሰልጣኞች ጫንቃ ላይ የሚያርፈው ጫናም በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም።

ከዚህ መነሻነት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሰንጠረዡ አጋማሽ በታች የሚገኙት አሰልጣኞች ከፍ ባለ ጫና ውስጥ እንደሚገኙ መገመት አያዳግትም። በተለይ ደግሞ የውጤት ቀውስ ላይ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በዚህ ረገድ ትኩረት የሚስብ ነበር። የድሬው አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን ጫና መኖሩን አምነው በጨዋታው ውጤት ካላስመዘገቡ አንድ ውሳኔ እንደሚኖር ጠቆም አድርገው የነበረ ሲሆን ጨዋታውን በድል ከተወጡ በኋላ በሰጡት አስተያየትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነበር።

“አንዳንዴ በእግር ኳስ ጥሩ ቡድን ሰርተህ ውጤት እምቢ ይልሀል። አንዳንዴ አንተ ገለል ስትል ውጤቱ ይመጣል።’ የሚል ጭንቅላቴ ውስጥ ሳብሰለስለው የነበረ ነገር ስላለ ዛሬ ብንሸነፍ በፍቃዴ ለመልቀቅ ወስኜ ነበር በራሴ። እንጂ ኃላፊዎቼ ያስጨነቁኝ ነገር የለም። እንደውም ትናንትም ከትናንት ወዲያም ደውለው ‘በርታ አይዞህ ጥሩ ቡድን ነው’ ነበር የሚሉኝ። ያው እግዚአብሔር ረዳኝ እና ወደ ዛሬ ማሸነፉ መጣሁ። ከዚህ በኃላ ያለውን ነገር ወደማስቀጠሉ ነው።” የሚል አስተያየት የሰጡት አሰልጣኝ ፍስሐ የተሸከምኩት ነገር ከባድ ነበር። ከዚህ መውጣታችን ከማጥ የመውጣት ያህል” ነው። ብለዋል።

ከጫና ጋር በተያያዘ የአዳማ ከተማው አስቻለው ኃይለሚካኤል የተለየ ሀሳብ ሰጥተዋል። አሰልጣኙ በቀጣይ ለሚመጡ ነገሮች ዝግጁ ስለመሆናቸው ነው የተናገሩት። “ጫና ሲባል አሰልጣኝ እኮ ይሰራል ይለቃል። ይሄ ያለ ነው፤ ለሁሉ ነገር ዝግጁ ነኝ። ባለህ አቅም ነው የምትወዳደረው። የመጀመሪያው ዙር ካለቀ በኃላ ለማስተካከል ጥረት ይኖራል። ግን ምንም አያስጨንቀኝም ፤ ባለህ አቅም ነው ወደ ውድድር የምትገባው። የሚመጣውን ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ፤ አዲስ ነገር አይኖርም።” ብለዋል።

👉የድቻን መንፈስ የለወጡት ዘላለም ሽፈራው

ከጥቂት ቀናት በፊት ወላይታ ድቻን በአሰልጣኝነት የተረከቡት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በእጅጉ ተዳክሞ የነበረውን ወላይታ ድቻን ነፍስ እየዘሩበት ይገኛል። በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ላይ ያስመዘገቡት ድልም በአጠቃላይ የዚህ ሂደት ማሳያ ነው።

አሰልጣኝ ዘላለም ኃላፊነቱ ከተረከቡ ወዲህ በአጠቃላይ ውጤት ማስመዝገብ ተስኖት የነበረውን ቡድን ለማነቃቃት የሞከሩት ኳስ ቁጥጥርን መሰረት አድርጎ ለመጫወት ይሞክር የነበረው ቡድን ላይ የጨዋታ አስተሳሰብ ለውጥን በማድረግ ነው። ምንም እንኳን በተከታታይ የገጠማቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጥንካሬ መነሻነት እንደሆነ ቢገመትም አሰልጣኞቹ በቀደሙት ቡድኖቻቸው እንደሚያስመለክቱን በወላይታ ድቻም ጠንካራ የመከላከል አወቃቀርን በመገንባት ረገድ አሰልጣኙ ያመጡትን ለውጥ በሁለቱ ጨዋታዎች በጉልህ መመልከት ይቻላል።

በቀላሉ ግቦችን ያስተናግድ የነበረው ቡድን አሁን ላይ እንደ ቡድን በጥንቃቄ ጠቅጠቅ ብሎ የሚከላከል እንዲሁም በወገብ በላይ በሚገኙ ተጫዋቾች ፍጥነት ደግሞ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለመጫወት እንደሚያስቡ ፍንጭን የሚሰጥ እንቅስቃሴ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያስመለከቱን አሰልጣኙ ተጫዋቾቻቸው በሀሳባቸው ተገዝተው መልካም የሆነ ግብረ መልስ እያሳዩ ይገኛል። እርግጥ ነው ከተወሰኑ ተጫዋቾች በስተቀር አብዛኛዎቹ የቡድኑ ተጫዋቾች አሰልጣኝ ዘላለም መከተል ለሚያስቡት የጨዋታ መንገድ የተሰሩ መምሰላቸው ሒደቱን ሊያቀልላቸው እንደሚችል ይገመታል።

ከአጨዋወት ለውጡ በላይ ወላይታ ድቻ ከመሳይ ተፈሪ ስንብት በኋላ ጎድሎት የቆየው ተነሳሽነት በተለይ በቡናው ጨዋታ ላይ አብቦ መታየቱ በወራጅ ቀጠናው ስጋት ላይ ለሚገኘው ቡድን ተስፋ የሚሰጥ ነው።

👉የካሣዬው ኢትዮጵያ ቡና ፈተና

በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ከሚገኙ ቡድኖች ከጨዋታ ጨዋታ የማይቀያየር በአሰልጣኙ በታመነበት በአንድ የጠራ ጨዋታ መንገድ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የሚሞክር ቡድን ነው። በዚህ መነሻነት ቡድኖች ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥሙ ወደ ኃላ አፈግፍገው በመከላከል ቡድን በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸው የተለመደ ነው። በዚህ የጨዋታ ሳምንት በወላይታ ድቻ ሲሸነፉም የተከሰተው ይህ ነው።

ኢትዮጵያ ቡና በሚከተሉት እንቅስቃሴ ውስጥ ኳስን በትዕግስት መቆጣጠር ከራሳቸው የሜዳ ከፍል ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት ወደ መሀል ሜዳው ከሚጠጉት ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ጀምሮ ሁሉም ተጫዋቾች በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ቁመትም ሆነ ስፋት ለመጠቀም በሚያስችል ሁኔታ ዘርዘር ብለው መገኘኘታቸው የግድ ነው።

በዚህ ሒደት በትዕግስት ኳስን በማንሸራሸር ከአንደኛ የሜዳ ጠርዝ ወደ ሌላኛው በመቀያየር ክፍተቶች ለመፍጠር መሞከር እንዲሁም የሜዳውን ጥልቀትን ሆነ ስፋት ለማጥቃት የሚታትረው ቡድን ኳሷ የቡድኑ ህልውና ነች። ቡድኑ በዚህ “ከፍተኛ ስጋት ከፍተኛ ውጤት” ባለው አጨዋወት ውስጥ ተጋጣሚ ቡድኖች ተከላክለው በመልሶ ማጥቃት እንዳያገኟቸው ለማድረግ ዋነኛው መንገድ ኳሱን በቀላሉ እንዳይነጠቁ ማለትም እንቅስቃሴያቸው በተደጋጋሚ እንዳይቋረጥ ማድረግ ተቀዳሚው መፍትሔ ነው።

በተሰረዘውም ሆነ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቡድኑ ካስተናገዳቸው አብዛኞቹ ግቦች መነሻም እነዚሁ በቀላሉ የሚባክኑ (የሚቆረጡ) ኳሶች ናቸው ፤ ስለዚህም ቡድኑ በተለይ በዚህ ረገድ የሚስተዋልበትን ችግር ለማስወገድ የሚታዩ ለውጦች ቢኖሩም ይበልጥ መስራት ይኖርባቸዋል።

በተጨማሪም ቡድኑ ኳስን በሚያጣበት ወቅት በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ እንዳለው የተጫዋች ብዛት በፍጥነት ኳስን ዳግም ለማግኘት(counter press) በማድረግ ኳስን መልሶ በማግኘት ረገድ በጣም ብዙ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮችን ማሻሻል ካልቻለ በመልሶ ማጥቃት የመሰበር ዕድሉ ከፍተኛ ነው።

ዓበይት አስተያየቶች

👉ዘርዓይ ሙሉ ስለ ስሜታዊ እንቅስቃሴዎቹ

“አንዳንድ ተጫዋቾቼ የሰጠኋቸውን ታክቲክ ሲተገብሩ አልነበረም። በተለይ ተቀይሮ የገባው እሱባለው በተደጋጋሚ ቦታውን ሲለቅ ነበር፣ የአቋቋም ችግር ነበር፣ ኳስ ለማስጣል የሚያርገው ጥረት ደካማ ስለነበር እሱ ላይ በተደጋጋሚ ስጮህ ነበር። በተጨማሪ ተከላካዮቼ እነሱ ኳሱን ካገኙት በኋላ ነበር ሲደርሱ የነበረው። በዛ ነው እየተነሳሁ መልዕክት ሳስተላልፍ የነበረው።”*

👉አብርሀም መብራቱ ስለ ተከታታይ የቀይ ካርድ እና የተጫዋቾች ሥነ-ምግባር

“የዲሲፕሊን ችግር የለም። ሁለቱም የወጡብን ተጫዋቾች ክለቡ ውሰረጥ ባላቸው ዲሲፕሊን በጣም የተመሰገኑ፣ የልምምድ ሰዓት አክብረው የሚሰሩ ተጫዋቾች ናቸው። ነገር ግን ሜዳ ውስጥ ውጤት ከመፈለግ አንፃር ባለ ጉጉት የሚወስዱት እርምጃ ለጉዳት ዳርጓቸዋል። ይህ እንደ ትምህርት የሚወሰድ ይሆናል።”

👉ማሒር ዳቪድስ ይዘውት የገቡትን የጨዋታ እቅድ በተጫዋች ጉዳት ስለመቀየራቸው እና በቡድኑ የዛሬው እንቅስቃሴ ደስተኛ ስለመሆናቸው

“አዎ በሚገባ። ይዘነው የገባነውን እቅድ ረብሾብናል። ውጤቱ አቻ ቢሆንም እንደጥቅሉ ስንመለከተው ግን እንደቡድን ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። በመጀመሪያዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርብን መውጣት ተስኖን ነበር ነገርግን አሁን በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ አላስተናገድንም ከዚያ አንፃር ከተመለከተነው ጥሩ የሚባል ነው።

” በትክክል መናገር የምችለው ነገር ቢኖር በትክክለኛው መንገድ ላይ እየተጓዝን ነው። መስራት የሚገባቸው ቀሪ ስራዎች ቢኖርም ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች እንደቡድን ጥሩ እየተንቀሳቀስን ነው።”

👉ሥዩም ከበደ ሰለ ሱራፌል ዳኛቸው

“አንደኛ እስካሁን ባደረግናቸው ጨዋታዎች የእሱ መልካም እንዲሁም ደካማ ጎኖች ነበሩ። እነዛን ከዚህ በፊት ቁጭ ብለን ማረም እና ማስተካከል እንዳለበት ተነጋግረናል። ዛሬ ደግሞ ይበልጥ ቁጭ ብሎ እንዲያየው አጠቃላይ እንቅስቃሴውን እንዲመለከተው ማድረጋችን ለእሱ እድል ሰጥቶታል። ሲገባም እንዳያችሁት በእርጋታ የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ መልካም ናቸው። ሱራፌል ትልቅ አቅም ያለው ጎበዝ ተጫዋች ነው ፤ ለክለብ እና ለብሔራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን ከሀገር ወጥቶም ለመጫወት የሚያስችል አቅም ያለው ተጫዋች ነው። ስለዚህ እነዚህን ጥቃቅን ነገሮችን እያስተካከለ መሄድ ይኖርበታል።”

👉ዘላለም ሽፈራው ስለ ኤልያስ አህመድ የመጀመሪያ አጋማሽ ለውጥ

” ቡና ኳስ መስርቶ እንደሚጫወት ይታወቃል። በመጀመርያ አጋማሽ በነበረን እንቅስቃሴም ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ነበር ለመጠቀም የፈለግነው። ከዚህ ቀደም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ይዘነው የገባነው አጨዋወት ጥብቅ መከላከል ነበር። ያ ግን ቡና ላይ አይሰራም የሚል ሀሳብ ስለነበረን ጫና በማሳደር መጫወት ነው የፈለግነው። ለዛ ደግሞ የአጥቂ አማካዩ ሚና ጉልህ ነበር። ሆኖም የፈለግነውን ነገር ከኤልያስ አላገኘንም። ለዛ ነው ቶሎ ቅያሪ ያደረግነው።”

👉ካሣዬ አራጌ ጎሎች ስላስተናገዱበት መንገድ

” ከኛ የአጨዋወት ባህርይ አንፃር እንዲህ አይነት ክፍተቶች ይፈጠራሉ። እንዲህ አይነት ክፍተት ሲፈጠር ተጋጣሚ እንዳይጠቀምበት ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ የመስራት ጉዳይ ነው። ወደፊትም እንዲህ አይነት ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የማንገኝበትን መንገድ አጠናክረን እስካልሰራን ድረስ። የመጀመርያው ጎል የተቆጠረበት መንገድ የመገባበዝ ነበር። አበበ ተክለማርያምን ሲጠብቅ ተክለማርያም አበበን ይጠብቃል። በዚህ መሐል ነው የነሱ አጥቂ ተጠቃሚ የሆነው። እንዲህ አይነት ነገሮች በእግርኳስ የሚያጋጥሙ ናቸው።”

👉አሸናፊ በቀለ ሀዋሳ ከተማን ሲገጥሙ ስለነበረው አካላዊ ጉሽሚያ

ጨዋታው አካላዊ ጉሽሚያዎች የበዙበት ስለነበረ ሁለታችንም በምንፈልገው መንገድ አልተጫወትንም። ከነበረው የተሻለ የኳስ ፍሰት ይኖራል የሚል ግምት ነበረን። ነገርግን ያሰብነውን ነገር ለመፈፀም አልቻልንም። በአጠቃላይ በጨዋታው ሁለታችንም ቡድኖች ያሰብነውን ተግብረን ተጫውተናል ብሎ መናገራቸውን ያስቸግራል።


© ሶከር ኢትዮጵያ