ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በዘጠነኛው ሳምንት የተመለከትናቸው ተጫዋች ነክ ጉዳዮችን በሚከተለው መልኩ አሰናድተናል።


👉ከረጅም ጊዜ በኃላ ወደ ሜዳ የተመለሱት ናትናኤል ዘለቀ እና ብሩክ ቃልቦሬ

ከ2005 አንስቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን እየተጫወተ የሚገኘው ናትናኤል ዘለቀ ባሳለፍነው ዓመት በልምምድ ወቅት ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ለረጅም ጊዜያት ከሜዳ መራቁ የሚታወስ ነው። ለህክምና ወደ ቱርክ አቅንቶ የተሳካ የቀዶ ጥገና አድርጎ የተመለሰው ተጫዋቹ ቡድኑ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ባደረገው የ8ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ላይ ከረጅም ጊዜያት በኃላ በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ የመጀመሪያውን ጨዋታ አድርጓል። ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን መጫወት የቻለው ናትናኤል ከረጅም ጊዜ ጉዳት እንደተመለሰ ተጫዋች መጥፎ የማይባል የጨዋታ ቀንን አሳልፏል።

በተመሳሳይ የቀድሞው የወላይታ ድቻ ፣ ወልዲያ ከተማ እና አዳማ ከተማ አማካይ የነበረው ብሩክ ቃልቦሬ ለአንድ ዓመት ገደማ ከሜዳ ከራቀ በኃላ በዚህ የጨዋታ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕና ከሀዋሳ ከተማ 0-0 በተለያየበት ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት የመጀመርያውን ጨዋታ ማድረግ ችሏል። በጉዳት ከጨዋታ እንደመራቁ ፈታኝ እና የአካል ብቃትን በጠየቀው የሆሳዕና እና ሀዋሳ ጨዋታ ላይ ጉዳት ያስተናገደው ተስፋዬ አለባቸውን በመተካት በመጀመርያው አጋማሽ እንዲገባ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የወሰኑት ውሳኔ ትኩረትን የሚስብ ጉዳይ ነበር።

👉ጨዋታውን ያነቃቃው ሹሬሳ ዱቢሳ

ሰበታ ከተማ በሲዳማ ቡና 1-0 በተረታበት ጨዋታ ግብ ያስተናገደው ሰበታ ከተማው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ኢብራሂም ከድርን አስወጥተው ወጣቱን ሹሬሳ ዱቢሳን ያስገቡበት ቅያሬ ምንም እንኳን የታለመለትን ግብ ባይመታም የጨዋታውን መንፈስ የቀየረ ነበር።

ፈጣኑ የመስመር አጥቂ በሜዳ ላይ በቆየባቸው ደቂቃዎች ፍጥነት ጎድሎት የነበረውን የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማፍጠን ረገድ ከፍተኛ ሚና ነበረው። እንዳለመታደል ሆኖ ወደ ግብነት ሳይቀየሩ ቀሩ እንጂ ሹሬሳ ሦስት ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችንም ማግኘት ችሎ ነበር።

የአዳማ ከተማ የእድሜ እርከን ቡድኖች ውጤት የሆነው ተጫዋቹ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባባቸው ጨዋታዎች የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት እጅግ አስገራሚ ነው።

👉ልቡ የተሰበረው ዳንኤል ኃይሉ

ሲዳማ ቡና በማማዱ ሲዲቤ ብቸኛ ግብ ሰበታ ከተማን በረታበት የ9ኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ በ80ኛው ደቂቃ ላይ የሰበታው አማካይ ዳንኤል ሀይሉ በሲዳማው ያስር ሙጌርዋ ለተሰራበት ጥፋት በተሰጠው አፀፋዊ ምላሽ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል። ታድያ በስሜታዊነት በወሰደው እርምጃ የቀይ ካርድ ሰለባ የሆነው ዳንኤል ከቀይ ካርዱ በኃላ ሁኔታውን ለመቀበል ተቸግር እጅግ በተሰበረ ልብ እያነባ ከሜዳ በጓደኞቹ እገዛ የወጣወበት መንገድ ትኩረት የሚስብ ነበር።

ከሜዳ ከወጣም በኃላ ከሜዳው የመውጫ ደረጃ ላይ ሆኖ ሲያለቅስ የነበረበት መንገድ የሳምንቱ አሳዛኝ ክስተት ነበር።

👉አስደናቂ የጨዋታ ቀን ያሳለፈው ፀጋዬ ብርሃኑ

ወደ ድል ለመመለስ ከተጫዋቹ አንዳች ምትሀትን ይጠብቅ የነበረው ወላይታ ድቻ ከተከታታይ ስድስት ጨዋታወዎች በኃላ ኢትዮጵያ ቡናን በመርታት ወደ ድል ሲመለስ ሁለቱንም ወሳኝ የማሸነፊያ ግቦች ያስቆጠረው ፀጋዬ ብርሃኑ ሚና የጎላ ነበር።

ከኳስ ውጪ እጅግ አስደናቂ በሆነ ታታሪነት ክፍተቶችን ለመጠቀም ጥረት ሲያደርግ የዋለው ፀጋዬ ቡድኑ ኳስ ሲያጣ እና ቡናዎች ከኋላ መስርተው ለመውጣት በሚሞክሩት ወቅት ለመከላከል የነበረው ፈቃደኝነት በጉልህ የሚታይ ነበር። በተለይ የመጀመርያውን ጎል ለማስቆጠር በተከላካይ እና ግብ ጠባቂ መሐል ተገኝቶ ያለመናበባቸውን ክፍተት የተጠቀመበት መንገድ የተጫዋቹን የተታታሪነት ባህርይ በሚገባ የሚያሳይ ነው።

በአጥቂያቸው ስንታየሁ መንግሥቱ ጉዳት የሳሳው የወላይታ ድቻ የአጥቂ መስመር ላይ ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ፀጋዬ ከወሳኙ የኢትዮጵያ ቡና ድል በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታን ያደረገው አጥቂው ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።

” የዛሬው ጨዋታ ያደረግነው በጣም በጫና ውስጥ ያለው ነበረ። ካለን ነጥብ አንፃር ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ጎል ተቆጥሮብን ነበር። ተጭነን መጫወት እንዳለብን ተነጋግረን ነበር ከዕረፍት በኃላ የገባነው ውጤቱም ተሳክቶልናል። የዛሬው ሦስት ነጥብ ለእኛ ለቀጣዩ ጨዋታ ስንቅ የሚሆነን በመሆኑ ውጤቱ በጣም ያስፈልገን ነበር። በዚህም በጣም ደስ ብሎኛል።”

👉ጨራሹ ሙኸዲን ሙሳ እና አባካኙ ጁንያስ ናንጂቡ

እንደ ቡድን በዝውውር መስኮቶቹ በርካታ ተጫዋቾችን ከማስፈረም በተወሰነ መልኩ ለወጥ ያለ አካሄድን ባለፉት ሁለት ዓመታት መከተል የጀመረው ድሬዳዋ ከተማ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ከእድሜ እርከን ቡድኖች በማሳደግ በቂ በሚባል ደረጃ ባይሆን የመጫወቻ ደቂቃዎችን እየሰጠ ይገኛል። ከዓመታት በፊት ረመዳን ናስርን ወደ ዋናው ቡድን ሲያስተዋውቁ አሁን ደግሞ ባለተራው ሙኸዲን ሙሳ ይመስላል።

ፈጣኑ የመስመር እና የፊት አጥቂ ሙኸዲን አስደናቂ ፍጥነቱ እና ከግብ ፊት ያለው እርጋታ ልዩ ያደርጉታል። በተሰረዘው የውድድር ዘመን ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ምን ማድረግ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠው ተጫዋቹ ዘንድሮ ደግሞ በሒደት በአሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን የቡድን ዝርዝር ውስጥ በቀዳሚነት ከሚሰየሙ ተጫዋቾች ተርታ መሰለፍ ችሏል። ተጫዋቹ ይህን በጥረቱ ያሳካወን የመጫወት እድል በሚገባ እየተጠቀመበትም ይገኛል። በዚህ ሳምንት ሁለት ግሩም ግቦችን ያስቆጠረው ሙኽዲን የዓመቱ ጎሎቹን ቁጥር 5 አድርሷል።

በተቃራኒው ከወልዋሎ ድሬዳዋ ከተማን የተቀላቀለው ናሚቢያዊው አጥቂ ጁንያስ ናንጂቡ ግን በአስደናቂ ፍጥነቱ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ሲያስጨንቅ ብሎም እድሎችን መፍጠር ቢችልም የመጨረሻ ውሳኔዎቹ ግን አሁንም ኢላማቸውን መጠበቅ እንደተሳናቸው ቀጥሏል።

እንደበርካቶቹ በሊጋችን እንደሚገኙ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው የአጥቂ ስፍራ ተሰላፊ ተጫዋቾች ፍጥነት እና ጉልበትን የታደለው አጥቂው እያመከናቸው የሚገኙት አስቆጭ እድሎች ቡድኑን ለችግር ሲዳርጉ ይስተዋላል። በዚህ ሳምንት ምንም እንኳን ቡድኑ ሌሎቹ የአጥቂ ስፍራ ተሰላፊዎች ላስቆጠሯቸው ግቦች አመቻችቶ በማቀበል ትልቆ ሚና ቢወጣም በዚህኛውም ሆነ ከዚህ ቀደም በነበሩት ጨዋታዎች ያባከናቸው ኳሶች በርካታ ነበሩ።

ተጫዋቹ ያለውን ፍጥነት እና ጉልበት ተጠቅሞ የሚፈጥራቸው የጎል ዕድሎች እንዲሁም የሚያመቻቻቸው ኳሶች በግልፅ በሚታይ መልኩ ድሬዳዋን እየጠቀመ ቢገኝም በተለይ ነጥብ ለማግኘት ፈታኝ በሆኑ ጨዋታዎች ላይ የሚገኙ ወርቃማ እድሎችን ወደ ጎል መቀየር ላይ ተግቶ መሥራት ከናሚቢያዊው አጥቂ የሚጠበቅ ነው።

👉የወጣቶቹ አበርክቶ በድቻ ድል ላይ

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ወላይታ ድቻን ከተረከቡ ወዲህ የተሻለ የመሰለፍ እድል እያገኘ የሚገኘው ቢኒያም ፍቅሬ እና ለቡድኑ የመጀመሪያውን ጨዋታ በቋሚነት የጀመረው መሳይ ኒኮል ለወላይታ ድቻ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት አይነተኛ ሚናን ተወጥተዋል።

ወጣቱ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች መሳይ ኒኮል በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ጨዋታ የጀመረ ቢሆንም ሚናውን በአግባቡ ሲወጣ ታይቷል። የቡናን ቅብብሎች በማቋረጥ ብሎም የመቀባበያ ቦታዎችን በመዝጋት የተሳካ ቀን ያሳለፈው መሳይ የአሰልጣኙን ዕምነት ካገኘ ወደፊት ተስፋ ከሚጣልባቸው አማካዮች አንዱ መሆኑን በጨዋታው አሳይቷል።

በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ቢንያም ፍቅሬ ቡድኑ አጥቶት የነበረውን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ስልነት እንዲያገኝ አስችሏል። በገባበት ቅፅበት በመጀመርያ ንክኪ ጎል ለማስቆጠር በእጅጉ ተቃርቦ የነበረው ቢንያም ለሁለተኛው ጎል በማመቻቸት ለድሉ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ጥቂት የማይባሉ ወጣቶችን በስብስቡ የያዘው ወላይታ ድቻ ከሁለቱ ወጣቶች በተጨማሪ መልካሙ ቦጋለ፣ መሳይ አገኘሁ እና አብነት ለገሰ ለመሳሰሉ ወጣቶችም የመጫወት ዕድል እየሰጠ ይገኛል።

👉 መሳይ አያኖ ሲዳማን ታድጓል

የውድድር ዘመኑን ከቡድኑ የተቀዛቀዘ አቋም ጋር በሚመሳሰል መልኩ ቀዝቃዛ አጀማመር ያደረገው መሳይ አያኖ በዚህ ሳምንት ድንቅ ጊዜ ካሳለፉ ተጫዋቾች አንዱ ነው። 

ሲዳማ ቡና ሰበታ ከተማን ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ድንቅ አቋሙን ያሳየው መሳይ የፍፁም ገብረማርያም ፍፁም ቅጣት ምትን ከማዳኑ በተጨማሪ የሰበታን ተደጋጋሚ ሙከራዎች ማክሸፍ ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ይዘው እንዲወጡ ጉልህ ሚና ተወጥቷል። 


© ሶከር ኢትዮጵያ