“ዕድሎች ባገኝ ምሳሌ የምሆንባቸው አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ” – ቴዎድሮስ በቀለ

በሀዲያ ሆሳዕና ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ የጀመረው እና በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ግዙፉ ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ለመጀመርያ ጊዜ ቆይታ አድርጓል።

ዶዶላ ከተማ የተወለደው ቴዎድሮስ በኦሮሚያ ምርጥ ውድድር ላይ ባሳየው አቋም ለአርሲ ነገሌ ተጫውቶ በማስከተል ለአዳማ ከተማ ተጫውቷል። በመቀጠልም ከብዙ የስፖርት ቤተሰብ ጋር ራሱን ያስተዋወቀበት እና የኢትዮጵያ ዋንጫን ያነሳበት መከላከያን በመቀላቀል ለአራት ዓመታት ተጫውቷል። እጅግ ከባድ ጉዳት ገጥሞት በእግርኳስ ህይወቱ ላይ ፈታኝ ጊዜ ቢያሳልፍም በመከላከያ ከተሳኩ ዓመታት ቆይታ አድጓል። ዳግም ወደ አዳማ ከተማ ተመልሶ ለሁለት ዓመት የተጫወተው ቴዎድሮስ ዘንንሮ በተቀላቀለበት ሀዲያ ሆሳዕና ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ሲሆን ከአይዛክ ኢሲንዴ ጋር ጥሩ ጥምረትን በመፍጠር በሀዲያ ሆሳዕና የኋላ ክፍል ሚናው እየጎላ መጥቷል። ግዙፉ ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ የጋር ለመጀመርያ ጊዜ ቃለ መጠይቅ አድርጎ ተከታዩን ሀሳብ አጋርቶናል።

ስለ ወቅታዊ አቋሙ

ዘንድሮ ያለሁበት ሁኔታ ጥሩ ነው። ከሰውነት ክብደት መጨመር ጋር ተያይዞ ትንሽ ተቸግሬ ነበር። ይሄን ለማስተካከል ጠንክሬ ስሰራ ነበር። አሁን ሁሉ ነገር ተስተካክሎ በጥሩ አቋም ላይ እገኛለው።

ስለ ጉዳቱ

ጉዳቴ በወቅቱ ትንሽ ከባድ ነበር። ያላሰብኩት ጉዳት ደርሶብኝ ስለነበሬ ቶሎ ህክምና ባገኝ ጥሩ ነበር። መከላከያ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፈ ስላልነበረ ተፅእኖ አድርገውብኝ መጫወቴ እጄ ሁለት ዓመት እየወለቀ ድጋሚ እየገባ ለመጫወት ተገድጃለሁ። በዚህም ምክንያት ብዙ የመጫወት እድል አምልጦኛል። አሁን ከጉዳቴ ሙሉ ለሙሉ አገግሜ በጥሩ ጤንነት ላይ እገኛለሁ።

የተለያየ ቦታ ስለመጫወቱ

በኢትዮጵያ እግርኳስ በተለያየ ቦታ መጫወትህ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል። ምክንያቱም በክለብህ የተለያየ ቦታ እየተጫወትክ ብሔራዊ ቡድን ላይ ምርጫ አይደርስህም። በመሐል ተከላካይ እና በመስመር ስትጫወት የምትተገብረው ሚና ይለያያል። ይህ ደግሞ በአንድ ቦታ ነጥረህ እንዳትወጣ ያደርገሀል። ለክለብህ ለአሰልጣኝ ታክቲክ ልትጠቅም ትችላለህ፤ ግን ራስህን ትጎዳለህ። ለምሳሌ አሰልጣኝ አሸናፊ በሴካፋ ዋንጫ ይዞኝ ሄዶ ሁሉንም ጨዋታ በመሐል ተከላካይ ቦታ ተጫውቼ ነው የመጣሁት። በጣም ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። እንዲያውም የውጭ እድል እስከማግኘት ደርሼ ነበር። ሆኖም ወደ መከላከያ ስመለስ በተለያየ ቦታ ያጫውቱኝ የነበረ በመሆኑ እጋጭ ነበር። ለምንድነው ጥሩ በሆንኩበት ቦታ የማታጫውቱኝ በማለት። ከክለቡ የወጣሁበትም ምክንያት በዚህ ነው። አሁን ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ። ጥሩ አቋም ላይም እገኛለው።

ስለ ትክክለኛ የመጫወቻ ቦታው

ለኔ ትክክለኛ ቦታ የምለው መሐል ተከላካይ ሆኜ ብጫወት ነው። ምክንያቱም እኔ ጋር ያሉ አቅሞች የመሐል ተከላካይ ሆኖ ለመጫወት የሚያስችሉ ናቸው። የግንባር ኳስ አጠቃቀም ጥሩ ነኝ፤ ሰውነቴም ለቦታው የተመቸ ነው። ስለዚህ የመሐል ተከላካይ ቦታ ላይ ብሆን በጣም እጠቅማለው።

ከወንድሙ የተለየ ቦታ የመጫወቱ ምክንያት

(እየሳቀ) አዎ! ዳግም ጥሩ አቅም ያለው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ነው። በጊዜ ሂደት የቦታ ለውጥ አድርጌ አሁን ወደ መከላከሉ ላመዝን እንጂ ከዚህ ቀደም በማጥቃቱ ላይ እጫወት ነበር።

ስለ ጫማ ቁጥሩ እና ግዝፈቱ

ግዝፈቴ በጣም ጠቅሞኛል። በቀላሉ ኳሶችን ለማስጣል እና ለማጨናገፍ እንዲሁም ለመሸፈን ይጠቅማል። ከተጠቀምክበት እኛ ሀገር ብዙ ስለሌለ አሪፍ ነው። የጫማ ቁጥሬ ያው 47 ነው። በጣም ትልቅ ቁጥር ነው። (እየሳቀ) ተፈልጎ ነው የሚገኛው። እኛ ሀገር እንዲህ ትልቅ ቁጥር የሚያደርግ የለም።

በመጨረሻ

አሁን ባለው ነገር አቅሙ አለኝ። ጥሩ ነገር አለኝ። ይህን ጠብቄ በመጫወት ክለቤንም ሀገሬንም ማገልገል እፈልጋለሁ። ሁሉን ነገሬን አውጥቼ መሥራት እፈልጋለሁ። ዕድሎች ባገኝ ምሳሌ የምሆንባቸው አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ