ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ያለ ጎል ተለያይተዋል

የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስረኛ ሳምንት በረፋድ ጨዋታ ቀጥሎ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅጣት ላይ የሚገኘው አስቻለው ታመነን በደስታ ደሙ ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሮቢን ንግላንዴን በአቤል ያለው እና አዲስ ግደይ ለውጦ ሲቀርብ ሲዳማ ቡና ሰበታን ካሸነፈበት ጨዋታ ግሩም አሰፋን በሰንደይ ሙቱኩ እንዲሁም ዳዊት ተፈራን በዮሴፍ ዮሐንስ በመለወጥ ወደ ሜዳ ገብቷል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በነበረው የማማሟቅ እንቅስቃሴ ላይ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በመጎዳቱ ፍቅሩ ወዴሳ ተክቶት ገብቷል።

ተደጋጋሚ የጨዋታ ውጪ እንቅስቃሴዎች፣ ጥፋቶች እና ጥቂት የጎል ዕድሎች የጨዋታውን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልፁ ሲሆን ሲዳማዎች ሙሉ ለሙሉ በመከላከል ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ክፍተት በመፈለግ ተጠምደው አርፍደዋል።

እጅግ የተቀዛቀዘ በነበረው የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጠንካራ ሙከራ ከክፍት ጨዋታ መመልከት ያልቻልን ሲሆን በ17ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ ተመስገን በጅሮንድ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣውና በተመሳሳይ ከማዕዘን ምት 21ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ተርፋ ሞክሮ ፍቅሩ ወዴሳ የመለሰበት የሚጠቀሱ የአጋማሹ ሙከራዎች ነበሩ።

ከዕረፍት መልስ የተሻለ መነቃቃት ባሳየው ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት የተሻሉ ለጎል መቅረብ ችለው የነበረ ሲሆን 61ኛው ደቂቃ ላይ ጊዮርጊሶች ኳስ ከኋላ ለማስጀመር ባደረጉት ቅብብል ለዓለም በአግባቡ ወደፊት ማሻገር ያልቻለውን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ አግኝቶ መትቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራ አስቆጪ ዕድል ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው የተጫዋች እና የአደራደር ለውጦች በማድረግ ተጭነው ለመጫወት ያደረጉት ጥረት እንደ መጀመርያ አጋማሽ ሁሉ በሙከራ ያልታጀበ ሆኗል። በ58ኛው ደቂቃ አዲስ ከመስመር የላከው ኳስ ሲመለስ ደስታ ደሙ አግኝቶት ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራም ብቸኛው ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ሲደርስ ተደጋጋሚ ጥፋቶች የበረከቱበት ሲሆን ፈቱዲን ጀማል የዳኛ ውሳኔ በመቃወም ከብሩክ የማነብርሀን ጋር በፈጠረው ንትርክ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። በቀሪ ደቂቃዎች በጎዶሎ የተጫዋቾች ቁጥር ለመጫወት የተገደዱት ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታቸውን አሸንፈው ለመውጣት የሚያስችል ወርቃማ ዕድል በመልሶ ማጥቃት ቢያገኙም ከሳጥኑ የግራ ክፍል ሆኖ ኳስ የተቀበለው ሀብታሙ ገዛኸኝ የመታውን ኳስ ለዓለም ይዞበታል። ጨዋታውም ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።




© ሶከር ኢትዮጵያ