የአሠልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-0 ሲዳማ ቡና

ያለ ግብ ከተጠናቀቀው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ማሒር ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በጨዋታው ደስተኛ ስለመሆኑ

በጨዋታው ሦስት ነጥብ ማግኘት እንችል ነበር። ግን የተጋጣሚያችን የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ጥሩ ነበሩ። በተለይ የመሐል ተከላካዮቹ የነበራቸው ብቃት ጥሩ ነበር። እኛም ግን ፊት አካባቢ ስህተቶችን ስንሰራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ ስለተከተለው የጨዋታ መንገድ…

ተጋጣሚያችን የመጫወቻ ቦታ ነፍጎን ነበር። የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች በቁጥር ብናበዛም ወሳኝ ቦታዎችን ዘግተውብን ነበር። እንደዛም ሆኖ ባገኘናቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ግብ ማግባት አልቻልንም።

ስለ ቀጣዩ የሆሳዕና ጨዋታ…

ሁሉም ጨዋታዎች ከባድ እና ፈታኝ ናቸው። ጨዋታውም ጥሩ ጨዋታ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በተለይ በጅማ ያለንን ቆይታ በጥሩ መንገድ ለማገባደድ እንጠቀምበታለን።

ስለ መጫወቻ ሜዳው…

መጫወቻ ሜዳው ለመጫወት በጣም የሚያስቸግር ነው። ኳስ ለመቀባበል፣ ተጋጣሚ ሳጥን ደርሶ ሙከራ ለማድረግ እና ለመሳሰሉት ሜዳው አስቸጋሪ ነው።

ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለ መሳይ ጉዳት እና ፈቱዲን ቀይ ካርድ

በእግርኳስ ያጋጥማል። በተለይ መሳይ ላይ የተፈጠረው ነገር ቡድናችን ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ምክንያቱም ተጫዋቹ ቋሚ ተሰላፊ ስለሆነ። ይህ ብቻ ሳይሆን ባልታሰበ ሰዓትም ነው የተጎዳው። ይህንን ተከትሎ መልበሻ ቤት እሱ ሲያለቅስ አይተው ሌሎቹም ተጫዋቾች አዝነው ሲያለቅሱ ነበር። ዞሮ ዞሮ ግን ተጫዋቾቹ ተነሳሽነት ፈጥረው ሜዳ ላይ የፈለግነውን እንቅስቃሴ አድርገናል። ተጫዋቾቼም በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ነበር። የሆነው ሆኖ ከሜዳው ነጥብ ይዘን ወጥተናል።

ቡድኑ ስለተከተለው የጨዋታ መንገድ…

የጊዮርጊስ የማጥቂያ አማራጭ ይሆናል ብለን ያሰብነው ሄኖክ ነው። በዚህም ሄኖክን ለማጥፋት ተመስገንን ተጠቅመናል። ከዛም እሱ ወጥቶ በዛው መስመር ለመጫወት አስበን ነገሮች ተሳክቶልናል። ከዚህ ውጪ እኛ አስቆጪ እድሎችን አምክነናል። እነሱ ያን ያህል ወደ እኛ ጎል አልደረሱም። እንደውም የአጨራረስ ችግር ባይኖርብን ኖሮ ጨዋታውን ማሸነፍ እንችል ነበር። በአጠቃላይ ግን የኋላ መስመራችን ጥሩ ነበር። ያገኘናቸውን እድሎች ያለመጠቀማችን ችግር ግን ለቀጣይ ጨዋታ እናስተካክላለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ