ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር እያጤነ ነው

ባለፉት ዓመታት የውጭ ሀገር አሰልጣኝ አልበረክትለት ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር እያጤነ መሆኑን ሰምተናል።

በተከታታይ ዓመታት ከዋንጫ የራቁት ፈረሰኞቹ ዘንድሮ 85ኛ ዓመታቸውን በሊጉ ዋንጫ በማጀብ ለማድመቅ በአፍሪካ እግርኳስ ልምድ ያላቸው ጀርመናዊው ኤርነስት ሚደንዶርፕን በሦስት ዓመታት ውል መቅጠራቸው ቢታወስም ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ውድድር ሳይጀምር አቋርጠው መሄዳቸው ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ በምክትል አሰልጣኝነት የመጡት ማሒር ዴቪድስ ቡድኑን ተረክበው በማሰልጠን መልካም የሚባል አጀማመር ቢያደርጉም አሁን ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ እንደማይገኙ ይታወቃል። ወቅታዊውን የውጤት ሁኔታ አስመልክቶ ለአሰልጣኙ ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው የሚታወቅ ሲሆን ዛሬ ደግሞ የስንብት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው እየተሰማ ይገኛል።

በአሁን ሰዓት ክለቡ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር እያጤነ ሲሆን የክለቡ የቦርድ አመራር ከዚህ ቀደም የሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ላለመቅጠር ካሳለፉት ውሳኔ አንፃር ዳግመኛ የውጭ አሰልጣኝ ሊቀጥር እንደሚችል የሚገመት ቢሆንም አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ምናልባት የሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ሊቀጠር እንደሚችልም ግምቶች እየወጡ ይገኛል።

ቡድኑ የጅማን ቆይታውን አጠናቆ ነገ ወደ አዲስ አበባ የሚያመራ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ