የአሳልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-3 አዳማ ከተማ

ከጨዋታው መጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞቹ ከሱፐር ስፖርት ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

ድሉ ስላለው ስሜት

ያው ሁሉንም ጨዋታ ለማሸነፍ ነው የምንገባው። በራሳችን ስህተት ነው ጎሎች የሚቆጠሩብን በአብዛኛው ጨዋታ። ተቃራኒ ቡድን ይዞ የመጣው ቀጥተኛ ኳስ ለመጠቀም ነበር። ያን ለማክሸፍ ሰሞኑን በነበረን የልምምድ ጊዜ አርመን ለመግባት ነው የሞከርነው። ያ ተሳክቶልናል።

ቡድኑ በሚፈልጉት መጠን ስለማጥቃቱ

አዎ ያየነውም ይሄንን ነው። ሁሉም ቡድን እዚሁ እየተገማገመ ነው ለሚቀጥለው ጨዋታ የሚዘጋጀው። ሀዋሳ ጠንካራ ቡድን ነው ፤ የተሟላ ቡድን ነው። ወጣቶች አብረው የቆዩበት ጥሩ ቡድን ነው። ያንን የእነሱን ጠንካራ ጎን አክሽፈን ውጤታማ የምንሆንበትን ስራ ነው ስንሰራ የነበረው ፤ ያ ተሳክቶልናል። ከዚህ በፊት ጉዳቶችም ነበሩ። አብዲሳ ጉዳት አጥቅቶት የነበረ ተጫዋች ነው ፤ ስገልፅ ነበር በፊትም። ሙሉ ሲሆን ግን ለሀገርም ሀብት ነው ፤ እንደገና ልጅ ነው። ፍሰሀም ልጅ ነው ከታች ነው የመጡት እና ጉዳት ላይ ነበሩ። በፊት የምናገረውም ያን ነበር። ባላን አቅም የምንሰበስባቸው ልጆች ተስፋ ሰጪዎች ናቸው።

ውጤቱን ጠብቀውት የነበረ ስለመሆኑ

አዎ! በቃ ለማሸነፍ ነው የገባነው። በዚህ አጋጣሚ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና የኦሮሚያ ስፖርት ኮሚሽን እንዲሁም የአዳማ አሰተዳደር ስፖርት ቢሮ አላፊ እና ኮሚሽነር ፍሰሀን እናመሰግናለን። ትልቅ መነቃቃት ነው መጥተው ያደረጉልን። የእነሱም አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም ለውጤታችን። ተጫዋቾቹም በቁርጠኝነት ነው የገቡት። የሚጎለብት ቡድን ነው። ጊዜ ፈጀብን እንጂ ያለዝግጅት የገባ ቡድን ነው። በሂደት ነው ልምድም በራስ መተማመንም የሚያገኙት። ዛሬ ተሳክቶልናል ከእግዚያብሔር ጋር ይሄንን ለማስቀጠል ነው።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

በእርግጥ ጨዋታው 3-1 ተጠናቋል። እኛም ካሰብነው በታች ነው የተጫወትነው። ያሰብነውን ለማድረግ ሞክረዋል። ክፍተቶች እና ችግሮች አሉብን። ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳናደርግ ያደረገን የራሳችን የተጫዋቾቻችን እንቅስቃሴ እንጂ ሌላ ምንም የከለከለን ነገር የለም። የራሳችን ችግሮች ናቸው። ሌላ የተለየ ምንም ነገር የለም።

ለመስመር ጥቃታቸው መዳከም የአዳማ የመከላከል ብቃት ምክንያት ስለመሆኑ

አይ አይመስለኝም። ዛሬ ከወትሮው የነበረን እንቅስቃሴ ጥሩ አይደለም። ሙሉ ቡድናችን ትክክል አይደለም። የእሱ ብቻ ሳይሆን የሚገቡትም ልጆችም እንደነሱ ባይሆንም የመሄድ አቅም አላቸው። ግን በጥቅሉ ጨዋታውን ራሱ መቆጣጠር አቅቶናል ዛሬ። ወይ ለክለቡ የሰጠነው ግምትም ሊሆን ይችላል። ያም ተፅዕኖ ሊያደርግ ይችላል። ከተጨዋቾቼ ጋር ተነጋግሬ ሜዳ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ቀርፈን እንመጣለን።

ውጤቱ እንዲህ ይሆናል ብለው ስለመጠበቃቸው

እውነት ለመናገር አልጠበኩትም። በጣም ብዙ ፉክክር ይኖረዋል ፤ እንሸነፋለን እግር ኳስ ነው ግን እንደዚህ ደግሞ ሆነን እንሸነፋለን ብዬ አልገመትኩም።


© ሶከር ኢትዮጵያ