የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-1 ሰበታ ከተማ

ከጨዋታው በኋላ የነበረው የአሰልጣኞች እና የሱፐር ስፖርት ቆይታ ይህንን ይመስላል።

አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው

ጨዋታው የታክቲክ ዲሲፕሊን ላይ ያተኮረ ነበር። ሁለታችንም ተመሳሳይ ፎርሜሽን ይዘን ነው የገባነው። ውጤቱን ለማምጣት ካለን ጉጉት ሁለታችንም ውጥረት ያለው ኳስ ነው። ግን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ አሻሽለን ሁለታችንም ሙከራዎች አድርገናል። ውጤት እንግዲህ በፔናሊቲ ገብቶብን ተሸንፈናል።

ቡድኑ የአቻ ውጤትን ስለመፈለጉ

አይ ! በሁለታችንም በኩል ጥንቃቄ ነበር ። ታች ስላለን ለማንሰራራት ካለን ፍላጎት ነው። ውጥረት ያለው ጨዋታ ነው ያልኩት ውጤቱን ከመፈለግ አንፃር ነው። በእያንዳንዱ ተጨዋች ውስጥ ደረጃውን ወደ ላይ ለማሻሻል ካለ ጉጉት ነው።

ስለኋላ ክፍሉ ክፍተት

ከዚህ በፊት እንዳያችሁት በራሳችን ጥቃቅን ስህተት ነበር ጎሎች የሚቆጠሩት። ያን ከደካማ ጎናችም ተነስተን እየሰራን ነው። ያን እያሻሻልን መጥተናል ያው ለውጦች አሉ ቡድናችን ላይ። የኃላ መስመሩም ቅርፅ እየያዘ ነው።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ስለድሉ ትርጉም

በተደጋጋሚ ከነበሩ አቻ እና ሽንፈቶች በኃላ ሦስት ነጥብ አግኝቶ ወደ ማሸነፍ መመለስ በተጫዋቾቻችን እና በአጠቃላይ በቡድኑ አባላት ሥነ-ልቦና ላይ የሚፈጥረው እገዛ ቀላል እይደለም። እና ወደ አሸናፊነት መመለሳችን ትልቅ ትርጉም አለው ለቡድናችን።

ስለቡድኑ ከሙከራ መራቅ

መጀመሪያ አጋማሽ ላይ የነበረውን መሀል ሜዳ ላይ የመወሰኑን ጉዳይ ማሸነፍ ስለነበረብን ይሄን ጨዋታ የተጋጣሚ ቡድን ሦስተኛ ክፍል ላይ ሲገቡ እንዲረጋጉ ነው የነገርናቸው። ግን ብዙ ጊዜ ማሸነፍ የሚፈልግ ቡድን ለማግባት ካለው ፍላጎት የተነሳ ብዙ የሚያባክናቸው ኳሶች አሉ። ከእነዚህ ዓይነት አላስፈላጊ ስህተቶች ከማሸነፉ ጋር ተዳምሮ እያስተካከልን እንሄዳለን ብዬ አስባለሁ።

ስለተጨዋቾቹ ትጋት

ዛሬ በጣም ! እንደውም ከሁሉም በላይ ከጉዳት እንደተመለሰ ሳይሆን ዳዊት ሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ልምዱን ተጠቅሞ ጥሩ ነገር ሰርተናል ብዬ አስባለሁ። በአጠቃላይ ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ድረስ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፎ ለመውጣት ልጆቼ ያደረጉት ተጋድሎ የሚደነቅ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ