ሀድያ ሆሳዕና የዕግድ ውሳኔ ተላለፈበት

በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና የተወሰነበትን ውሳኔ ተግባራዊ ባለማድረጉ ምክንያት ፌዴሬሽኑ የዕግድ ውሳኔ አሳልፎበታል።

ከባለፉት ዓመታት ደካማ የውድድር አፈፃፀም ዘንድሮ በሁሉም መልኩ ተሽሎ የመጣው ሀድያ ሆሳዕና ምንም እንኳን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለዋንጫ የሚገመት ቡድን ቢሆንም ከሜዳ ውጭ ያሉበት የተለያዩ ችግሮች በጉዞው ላይ ፈተና እየሆኑበት መምጣታቸው ይታወቃል።

አሁን ደግሞ ያሳለፍነው ዓመት የቡድኑ ተጫዋች የነበረው አብዱልሰሚድ አሊ ‘የደሞዝ ክፍያ አልተከፈለኝም’ በማለት ያቀረበውን ክስ ተከትሎ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ለተጫዋቹ ደመወዙ እንዲከፈለው በማለት ውሳኔ ቢያስተላልፍም ክለቡ ይህን ተግባራዊ ባለማድረጉ በቀረበ አቤቱታ ፌዴሬሽኑ ሀድያ ሆሳዕናን ከማንኛውም አገልግሎቶች የታገደ መሆኑን በደብዳቤ አሳውቋል።

በቀጣዮቹ ቀናት የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዕረፍት ላይ ስለሚቆይ ክለቡ ክፍያውን ፈፅሞ ጨዋታ ሳያልፈው ወደ ውድድር እንደሚመለስ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ