ሪፖርት| ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የከሰዓት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማን በማሸነፍ ከሦስት ተከታታይ አቻዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ከተጋራው ቡስብስብ ውስጥ ሦስት ለውጦችን በማድረግ አብዱልከሪም መሐመድ ፣ የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ ጨዋታውን ሲጀምሩ አማኑኤል ተርፉ ፣ ሀይደር ሸረፋ እና አዲስ ግደይ አራፊ ሆነዋል። አዳማም በሰበታ ከተማ ከተሸነፈው ስብስብ በተመሳሳይ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ዳንኤል ተሾመ፣ እዮብ ማቲያስ እና ጀሚል ያዕቆብን በታሪክ ጌትነት፣ አካሉ አበራ እና በላይ ዓባይነህ ምትክ ተጠቅሟል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኳስ ቁጥጥር ተሽለው በታዩበት የመጀመርያ አጋማሽ ወደ አዳማ የጎል ክልል ተጠግተው ቢጫወቱም ግልፅ የጎል ዕድሎች የፈጠሩባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። ያም ሆኖ ጌታነህ ከበደ በ10ኛው ደቂቃ ከርቀት አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ ከወጣበት ሙከራ ስምንት ደቂቃዎች በኋላ የመጀመርያ ጎላቸውን አግኝተዋል። በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ጨዋታ የጀመረው አቤል እንዳለ ከግራ የሜዳው ክፍል ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ሳጥን በመጠጋት የመታው ኳስ ከመረብ አርፎ ፈረሰኞቹን መሪ አድርጓል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ባሉት ደቂቃዎች ኳስ ከማንሸራሸር የዘለለ የጎል ሙከራ ያልተመለከትን ሲሆን በ32ኛው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሪነታቸውን የሚያሰፉበት ጎል አስቆጥረዋል። ከግራ መስመር አማኑኤል ገብረሚካኤል ያሻገረውን ኳስ ግቦ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ በአግባቡ ባለመቆጣጠሩ ጌታነህ ከበደ በአግባቡ ተጠቅሞ አስቆጥሯል።

አዳማዎች ከሌላው ጊዜ በተሻለ ለማጥቃት አመቺ የሆነ ስብስብ ይዘው ወደሜዳ ቢገቡም በዚህ አጋማሽ ለተጋጣሚያቸው ፈተና የሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራም ማድረግ አልቻሉም።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተለየ ባልተነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመስመር በኩል ጥቃት በመሰንዘር የጎል መገናቸውን ለማሳደግ ጥረት አድርገዋል። በ48ኛው ደቂቃ አማኑኤል ከአብዱልከሪም የተሻገረለትን ኳስ ወደ ጎል መትቶ የጎሉን ቋሚ ገጭታ የወጣችበት ሙከራም የምትጠቀስ ነበረች።

በክረምቱ ከመቐለ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው አማኑኤል ገብረሚካኤል በፈረሰኞቹ መለያ የመጀመርያ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል። በ59ኛው ደቂቃ ከጌታነህ የተመቻቸለትን ኳስ በጥሩ አጨራረስ የጎል ልዩነቱን ወደ ሦስት ያሳደገች ጎል አስቆጥሯል።

ከሦስተኛው ጎል መቆጠር በኋላ ጨዋታው ላይ መቀዛቀዝ ታይቶ የነበረ ቢሆንም አዳማዎች በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ያስቆጠሯቸው ጎሎች ጨዋታው ላይ ነፍስ እንዲዘራ አስችሎታል። በ69ኛው ደቂቃ ደሳለኝ ደባሽ ከርቀት የጣለለትን ኳስ ፍስሐ ቶማስ ከጊዮርጊስ ተከላካዮች ጋር ታግሎ ከሳጥኑ ጠርዝ በመምታት ሲያስቆጥር በ73ኛው ደቂቃ በቃሉ ገነነ በጥሩ ሁኔታ ወደፊት ይዞት የሄደውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ፀጋዬ ባልቻ ተቀብሎ የግብ ጠባቂውን አቋቋም በመመልከት በጥሩ ሁኔታ ከግራ የሳጥኑ ክፍል መትቶ አስቆጥሯል።

መሪነታቸው በደቂቃዎች ልዩነት የጠበበባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳሱን በመቆጣጠር ከጎሎቹ በኋላ ተነሳሽነት ያሳዩት አዳማዎችን እንቅስቃሴ መግታት የቻሉ ሲሆን በ88ኛው ደቂቃም መሪነታቸውን አስተማማኝ ያደረገች ጎል አስቆጥረዋል። ጌታነህ ከበደ የመታው ቅጣት ምት በግብ ጠባቂው እና አግዳሚው ሲመለስ ጥሩ ቀን ያሳለፈው አማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ