ወላይታ ድቻ ተጨማሪ ሦስት ተጫዋቾች ለማስፈረም ተስማማ

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የተለያዩ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በሚያደርጉት ጥረት ቀጥለው ሦስት ተጫዋቾችን ለማስፈረም መስማማታቸው ታውቋል። ክለቡም ወደ ውጪ ተጫዋቾች በድጋሚ ፊቱን መልሷል።

ወላይታ ድቻ ከነበረበት የውጤት መንሸራተት በአንፃራዊነት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ከቀጠረ በኃላ እያንሰራራ መምጣቱ ይታወቃል። ቡድኑ ክፍተት አለበት በተባለባቸው ቦታ ላይ ከሳምንት በፊት አስናቀ ሞገስ እና ዮናስ ግርማይን ለማስፈረም እንደተስማማ የሚታወስ ሲሆን አሁን ከሦስት ተጫዋቾች ጋር ተስማምቷል። በሦስት ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የውጪ ዜጋ ተጫዋች ለመጠቀምም ተቃርቧል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከጅማ አባጅፋር ጋር ድንቅ የሚባል ቆይታ የነበረውና ቡድኑ በ2010 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ የጎላ ድርሻ የነበረው ዓምና ከሰበታ ከተማ ጋር ቆይታ ያደረገው የቀድሞው የዓለም ወጣቶች ዋንጫ አሸናፊ ጋናዊው ዳንኤል አጃይ በክረምቱ ወደ መቐለ ለማምራት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም በወቅታዊው ችግር ምክንያት ለቡድኑ ሳይጫወት ቀርቷል። አሁን ደግሞ የወላይታ ድቻ የግብ ክልልን ለመምራት ወደ ሶዶው ክለብ አምርቷል።

ከአራት ዓመት በፊት ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ፈርሞ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው እና በጅማ አባ ጅፋር እና ስሑል ሽረ በቆየባቸው ጊዜያት ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው ታታሪው አይቮርኮስታዊ የመስመር አጥቂ ዲዲዬ ለብሪ ወላይታ ድቻን ለመቀላቀል የተስማማ ሌላው ተጫዋች ነው። በፊት መስመሩ የአማራጭ እጥረት ላለበት ቡድንም ጥሩ ዝውውር እንደሚሆን ይገመታል።

ሌላኛው ከሰምምነት የደረሰው ተጫዋች ከስሑል ሽረ ሁለተኛ ቡድን ተገኝቶ ላለፉት ዓመታት ከክለቡ ጋር ቆይታ የነበረውና በክረምቱ ለመቐለ 70 እንድርታ ፈርሞ የነበረው አማካዩ ነፃነት ገብረመድኅን ነው። ነፃነት የመከላከል ክፍል ሽፋን በመስጠት እና በማጥቃት ሒደት በማስጀመር በተለይ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየ ተጫዋች ነው።

ዳንኤል አጄይ እና ዲዲዬ ለብሪ በቅርቡ ከትውልድ ሀገራቸው በመምጣት ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነፃነት ገብረመድህን በአሁኑ ወቅት በወላይታ ሶዶ ከተማ ከቡድኑ ጋር አብሮ ልምምድ እየሰራ መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል።

ቅድመ ስምምነቶቹ መጋቢት ላይ የዝውውር መስኮት ሲከፈት በይፋ እንደሚፀድቁ ሲጠበቅ ወላይታ ድቻ በ2010 የውድድር ዓመት ቶጓዊው ጃኮ አራፋት፣ ቻዳዊው ማሳማ አሴልሞ እና ናይጄርያዊው ኢማኑኤል ፌቮን ከተጠቀመ ወዲህ የውጪ ዜጋ ተጫዛቾችን ለመጀመርያ ጊዜ የሚጠቀም ይሆናል።

በሌላ ዜና አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በቡድኑ ውስጥ ብዙም ሚና የሌላቸውን አስራ አንድ ተጫዋቾችን ለመቀነስ መወሰናቸው ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ