የጋቶች ፓኖም ማረፊያ ታውቋል

በሀገር ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጭ በመጫወት የምናውቀው ግዙፉ አማካይ ጋቶች ፓኖም ወደ ኢትዮጵያ ክለብ ተመልሶ ለመጫወት ተስማቷል።

በኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው ጋቶች ቡናማዎቹን ከለቀቀ በኋላ ወደ ሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ አምርቶ ብዙም ቆይታን ሳያደርግ ወደ ሀገር ውስጥ ተመልሶ በመቐለ 70 እንደርታ ስድስት ወራትን ከቆየ በኋላ በግብፆቹ ኤል ጎውና እና ሀራስ ኤል ሁዳድ እንዲሁም ወደ ሳውዲ አረቢያ ዲቪዥን ሁለት ክለብ አል-አንዋር አምርቶ መጫወቱ ይታወቃል።

ጋቶች በዛሬው ዕለት ከወላይታ ድቻ ጋር ቅድመ ስምምነት ማድረጉ የታወቀ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ቡድኑን ለመቀላቀል አርባምንጭ ኤርፖርት ደርሷል። ከሰዓት ከቡድኑ ጋር ልምምድ በመስራት ቆይታ ካደረገ በኃላ ቅድመ ስምምነቱ መጋቢት ወር ሲፀድቅ ወደ ጨዋታ እንደሚመለስ ለማወቅ ችለናል።

ይህ ከፍተኛ ልምድ ያለው ግዙፉ አማካይ ለወላይታ ድቻ ለመጫወት መስማማቱ ለቡድኑ መልካም ዜና እንደሚሆን ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ