ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ| መከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና አሸንፈዋል

ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የምድብ ሀ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ አሰላ አረንጓዴ ስታዲየም ላይ ሲካሄዱ መከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና ድል አድርገዋል። ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ ያለ ጎል ተጠናቋል።

በጠዋት ሦስት ሰዓት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ ያገናኘው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር አስተናግዶ ያለ ጎል ተጠናቋል። ያለፉትን ዓመታት ጠንካራ ወላይታ ድቻ በመገንባት ተፎካካሪ ቡድን የሰሩት አሰልጣኝ ተመስገን ዘንድሮም በታክቲክ አቀባበልም ሆነ የመጫወት ፍላጎታቸው ከፍተኛ የሆነ በህብረት አጥቅተው በጋራ የሚከላከል ጥሩ ቡድን ይዘው መቅረብ መቻላቸውን ተመልክተናል። 

በተመሳሳይ የቀድሞ የሲዳማ ቡና ተጫዋች የነበረው ወንድማገኝ ተሾመ ጥሩ ቡድን ሰርቶ የመጡ መሆናቸውን በጨዋታው እንቅስቃሴ መመልከት ችለናል። ጨዋታው የደርቢነት ስሜት የነበረው በመሆኑ ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክር ብንመለከትም በተደጋጋሚ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የሚሰሩ ጥፋቶች የጨዋታውን ፍጥነት እንዲቀዘቅዝ አድርጎት ጎል ሳንመለከትበት ተጠናቋል።

05:00 በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከመከላከያ አገናኝቶ በመጨረሻው ደቂቃ በመከላከያ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል አንድ ለዜሮ እንዲያሸንፍ አስችሎታል።

ጥሩ ኳስ የሚጫወቱት መከላከያዎች ሀዋሳ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም ያገኘውን አጋጣሚ አለመጠቀም ለማሸነፍ የመጨረሻውን ደቂቃ ለመጠበቅ አስገድዷቸዋል። በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማ ከዚህ ቀደም በምናውቀው አጨዋወትም ሆነ በግል ነጥረው በሚወጡ አጥቂዎቹ አማካኝነት ውጤት ይዞ የሚወጣውን ስብስብ በዚህ ቡድን ውስጥ አልተመለከትንም። ያም ቢሆን ጎሎች እንዳያስተናግዱ የተከላካዮቹ ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት የቡድኑ ጥንካሬ ነበር። 

የእንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው መከላከያዎች ከዕረፍት መልስ የሀዋሳው ተከላካይ ታምራት ተስፋዬ በግልፅ በእጅ በመማታቱ ምክንያት የዕለቱ ዳኛ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሲያሳዩት የዳኛውን ውሳኔ ከማክበር ይልቅ ውሳኔውን የተቃወበት መንገድ እንዲሁም ከሜዳ አልወጣም በማለት ያሳየው ያልተገባ ባሀሪ ፍፁም ሊታረም የሚገባ እና መደገም የሌለበት ተግባር ነው።

የቁጥር ብልጫውን ተጠቅመው በተደጋጋሚ ተጭነው በመጫወት ጎል ፍለጋ ያደረጉት ጥረት በ86ኛው ደቂቃ ተሳክቶላቸው ተሾመ በላቸው ከመከላከያ የሜዳ ክፍል የተጣለለትን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ አፈትልኮ በመውጣት ከርቀት የግብጠባቂውን አቋቋም አይቶ ኳሷን በአናቱ ላይ አሻግሮ ግሩም ጎል አስቆጥሩ መከላከያ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ጎል ጣፋጭ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ አስችሏል።

የዕለቱ የመጨረሻ ተጠባቂ ጨዋታ ዘጠኝ ሰዓት በሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና አገናኝቶ ሲቀጥል ቡናዎች በአጥቂው ከድር ዓሊ ብቸኛ ጎል አሸናፊ ሆነዋል። ተመጣጣኝ ፉክክር በተመለከትንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለይ በአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የሚፈጥሩት አደጋ ከባድ ነበር። የዚህ ሂደት አካል የሆነ ጎል በ18ኛው ደቂቃ ያለፉትን አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲሰለጥን የቆየው እና የወደፊት ምርጥ አጥቂ እንደሚሆን የሚጠበቀው ከድር ዓሊ ከአማኑኤል አድማሱ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ፊት በመግባት ከግብጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ለቡናማዎቹ ጎል አስቆጥሯል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት ግልፅ የጎል ዕድል ያልፈጠረ በመሆኑ ሊሳካ ያልቻለ መሆኑን ተመልክተናል። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ዛሬ ስኬታማ በሆኑበት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ተጨማሪ ጎሎችን ለማስቆጠር ዕድሉን አግኝተው የነበረ ቢሆንም የፈረሰኞቹ ግብጠባቂ ዳዊት በኃይሉ አምክኖባቸዋል።

ወደ ጨዋታው መጠናቂያ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው አንበል ኤፍሬም ታደሰ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። በቀረው ደቂቃ የቁጥር ብልጫውን ተጠቅመው የአቻነት ጎል ፍለጋ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጥረት ቢያደርጉም የተሳካ ሳይሆን ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ