ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ለ እና ሐ አስረኛ ሳምንት የመጀመርያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ እና ሐ ዛሬ በተደረጉ የአስረኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀጥል በምድብ ለ ነቀምቴ ከተማ፣ ሶዶ ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ፣ በምድብ ሐ ደግሞ ነገሌ አርሲ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

ነቀምቴ ከተማ እና ካፋ ቡና ረፋድ 4፡00 ላይ ተገናኝተው በመጨረሻም በነቀምቴ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ብዙም ለዕይታ ማራኪ ባልነበረው ጨዋታ የተሳኩ የቅብብል ሂደቶችን መመልከት ባንችልም ነቀምቴዎች ግብ ለማስቆጠር የነበራቸው ጥረት ግን የተሳካ ነበር፡፡ በተለይ በረጃጅም ወደ ፊት ተስቦ በመጫወት ሲያደርጉት የነበረው ትጋት ጎል እንዲያስቆጥሩ አስችሏቸዋል፡፡ 

28ኛው ደቂቃ ላይ የካፋ ቡናው ዳዊት ታደሰ በሳጥን ውስጥ በይርጉ አርጌሳ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አስቻለው ኡታ ከመረብ አሳርፎ ነቀምትን መሪ አድርጓል፡፡ ከጎሉ በኃላ በመልሶ ማጥቃት ካፋዎች ለመጫወት ቢሞክሩም አቅዳቸው ግን ስኬታማ መሆን አልቻለም፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ በነበረው ሙቀታማ አየር የተነሳ በእንቅስቃሴ የጎሉ አልያም ልንጠቅሳቸው የምንችላቸውን አጋጣሚዎች ለመመልከት ባንታደልም ነቀምቶች ያገኙትን አንድ ጎል በዚህኛው አጋማሽ አስቆጥረው ጨዋታው 2 ለ 0 በነቀምት አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ሁለተኛዋን ጎልም ምኞት ማርቆስ ነበር ለክለቡ ያስቆጠረው፡፡

8፡00 ሲል በቀጠለው የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ በቤንችማጂ ቡና እና ሶዶ ከተማ መካከል ውጥረት የነገሰበት ፍልሚያ ተካሂዶ ሶዶ ከተማ ድል አድርጓል። ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ መመልከት የቻልንበት ቢሆንም ደካማ የአጨራረስ አቅም ይታይባቸው ስለነበረ የተገኙትን መልካም አጋጣሚዎች ሲያመክኑ ተስተውሏል፡፡ ለዚህም ማሳያ የቤንችማጂው አምበል ወንድማገኝ ኪራ 10ኛው ደቂቃ ላይ ብቻውን ከጎል ጋር ተገናኝቶ ያልተጠቀመባት ተጠቃሿ ሙከራ ነች፡፡ ሶዶ ከተማዎች በበኩላቸው 34ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት በጥላሁን ቦቶ አማካኝነት የተመታች ኳስ የግቡ ቋሚ የመለሰባቸው ሌላኛው አስቆጪ የሶዶዎች ዕድል ነች፡፡ ክለቦቹ ካደረጉት መልካም እንቅስቃሴ አንፃር ጎሎችን በቀላሉ በዚህኛው አጋማሽ እንመለከታለን ብለን ብንጠብቅም ያለ ጎል ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ለሶዶ ከተማዎች የተሳካ አጋማሽ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን በማድረጉ ሁለቱም ክለቦች የተዋጣላቸው ቢሆኑም የሶዶ ከተማ የመጨረሻ ደቂቃ ተነሳሽነት ሦስት ነጥቦችን እንዲያሳኩ አስችሏቸዋል፡፡ 83ኛው ደቂቃ ላይ በግምት 35 ሜትር ርቀት ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ቁመተ ረጅሙ ተከላካይ ርኆቦት ሰለሎ አክርሮ በመምታት ከመረብ አሳርፎ ሶዶን መሪ አድርጓል፡፡ ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ በቀሩት ደቂቃዎች እጅጉን ለመዳከም የተገደዱት ቤንች ማጂዎች በጭማሪ ደቂቃ ሰለሞን ጌታቸው ሁለተኛውን ጎል ለክለቡ አስቆጥሮ በወላይታ ሶዶ ከተማ አሸናፊነት ተፈፅሟል፡፡

10፡00 ላይ ሻሸመኔ ከተማን ከ ጋሞ ጨንቻ ያገናኘው ጨዋታ በሻሸመኔ አሸናፊነት ተጠናቋል። በሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ የአሰልጣኝ ማቲዮስ ለማው ክለብ በእንቅስቃሴም ሆነ በሙከራ ረገድ የተሻሉ ሆነው የታዩ ቢሆንም ፍፁም ደካማው የአጨራረስ ብቃታቸው ግን ኃላ ላይ ዋጋ ያስከፈላቸው ነበር። በተለይ አጥቂው ዘላለም በየነ የሚያገኛቸውን ኳሶች ወደ ጎልነት ለመቀየር ያደረጋቸው ጥረቶች ደካማ በመሆናቸው ጎል ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል።

ከእረፍት መልስ 47ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዮች በሰሩት ስህተት ሻሸመኔዎች ወሳኝ ጎል አስቆጥረዋል፡፡ ከመሀል ሜዳ በረጀሙ የተሻገረለትን ኳስ ማናዬ ፋንቱ ብልጠቱን በመጠቀም አግኝቶ በድንቅ አጨራረስ ከመረብ አሳርፎ በመጨረሻም ሻሸመኔ ከተማን 1ለ0 አሸናፊ አድርጓል፡፡

ምድብ ሐ

ጠዋት 3:00 ላይ ቂርቆስ ክፍለከተማን ከ ባቱ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ሁለት አቻ ተጠናቋል። ቢንያም ገሰሰ ለቂርቆስ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆክሮ ገና በአምስተኛው ደቂቃ መሪ ቢሆኑም ፍሬው ዓለማየሁ እና ጌታሰጠኝ ሸዋ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ባቱ ከተማዎች እስከ መገባደጃው መምራት ችለው ነበር። ሆኖም መድሀኔ ካሳዬ በ86ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ቂርቆስን ነጥብ አጋርታለች።

አራት ሰዓት ላይ ስልጤ ወራቤን የገጠመው ነገሌ አርሲ 1-0 አሸንፏል። ጨዋታው ጎል ሳይቆጠርበት መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እስኪጠናቀቅ የቆየ ሲሆን በጭማሪ ደቂቃ ሙሉዓለም በየነ ያስቆጠረው ጎል አርሲን አሸናፊ አድርጓል።

በምድቡ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ መሪው አርባምንጭ ከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ ተገናኝተው ያለ ጎል ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ