ናይጄሪያዊው አጥቂ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ለመጫወት ተስማማ

የ2010 የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ  ኦኪኪ አፎላቢ ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሚጫወትበትን ስምምነት ፈፅሟል።

በ2010 ከጅማ አባጅፋር ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው ናይጄሪያዊው አጥቂ ከዋንጫው ባሻገር በዛኑ ዓመት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ካጠናቀቀ በኋላ አወዛጋቢ በሆነ መልኩ ጅማን ለቆ ወደ ግብፁ እስማኤሊ ቢያመራም ጥቂት ጊዜን ብቻ አሳልፎ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለጅማ መጫወት የቻለ ሲሆን በተሰረዘው የውድድር ዓመት ደግሞ በመቐለ 70 እንደርታ ሲጫወት መቆየቱ ይታወሳል።

ኦኪኪ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ምክንያት ወደ ሀገሩ ተመልሶ የነበረ ሲሆን በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ለሲዳማ ቡና ለመጫወት ተስማምቷል። በዚህ ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው አጥቂው በቀጣይ ሳምንት በሚከፈተው የዝውውር መስኮት በይፋ ሲዳማ ቡናን እንደሚቀላቀል ሲጠበቅ በጅማ አባ ጅፋር እና ከመቐለ 70 እንደርታ አብረውት ከሰሩት አዲሱ የቡድኑ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር በድጋሚ የመገናኘት ዕድል የሚያገኝ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ