ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ድሬዳዋ ከተማ የንግድ ባንክን ተከታታይ የድል ጎዞ ገቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 11ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ በመለያየቱ ከተከታታይ ማሸነፍ በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጥብ ጥሏል፡፡

ከጨዋታው አስቀድሞ በሴቶች እግር ኳስ ላይ እየሰራች የምትገኘው ትዕንግርት የሴቶች ስፖርት የአንደኛውን ዙር ምርጦች ላላቸው ለአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው፣ ረሂማ ዘርጋው እና ለአረጋሽ ካልሳ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት በአዘጋጁ ዳዊት ሀብቴ እና በተጋበዙ እንግዶች ተበርክቶላቸዋል። ብዙሀኑ ከጠበቀው ግምት አንፃር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከታታይ ካሳዩት ውጤት መነሻነት በቀላሉ ያሸንፋሉ የሚል እምነት የነበራቸው ቢሆንም ፍፁም መሻሻል አሳይቶ የቀረበው ድሬዳዋ ከተማ ግን በሙሉ ዘጠና ደቂቃ የሚቀመስ አልነበረም። ግልፅ የጨዋታ የበላይነት ባልታየበት ጨዋታ ቡድኖቹ በተለያዩ መንገዶች የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ ታይቷል። በተለይ የአሰልጣኝ ብዙአየው ጀምበሩ ድሬዳዋ ከተማ ረጃጅም ኳሶችን በቀኝ አልያም ወደ ፊት መስመር ለታደለች አብርሀም እና ትንቢት ሳሙኤል በማሻገር ከወትሮው መዳከም የታየበትን የባንክ የተከላካይ ክፍል ሲረብሹ ተስተውሏል፡፡

10ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ከቀኝ የማዕዘን ምት በቀጥታ ወደ ጎል መታው የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰባት አጋጣሚ ንግድ ባንኮች በተጋጣሚያቸው ቢፈተኑም ሙከራን በማድረጉ ቀዳሚ ስለ መሆናቸው ማሳያ ነበር፡፡ በመስመር ባዘነበለው የንግድ ባንኮች የጨዋታ መንገድ በቀኝ መስመር ተከላካዩዋ ብዙነሽ ሲሳይ አማካኝነት ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም የድሬዳዋ ተከላካዮች ጥንካሬ ከተጫዋቿ የሚነሱ ኳሶች ሎዛ አበራ እና ረሂማ ዘርጋው ጋር እንዳይደርሱ አድርጓል፡፡መነሳሳት እና ይበልጥ በረጃጅም ኳስ ቶሎ ቶሎ ወደ አጥቂ ክፍሉ ለማድረስ ሲታት የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከቅጣት ምት ፀጋነሽ ወራና አክርራ መታ ምህረት ተሰማ እንደምንም ያዳነችባት ድሬዳዋዎች ላደረጉት ጥቃት ማሳያ ነበር ማለት ይቻላል፡፡አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ሰናይት ቦጋለ ከርቀት መታ ሂሩት ደሴ የያዘችባት ሌላኛው የንግድ ባንኮች ሙከራ ነበረች፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ አሁንም ብርቱ ፉክክር የታየበት ሆኖ ተጉዟል፡፡በሚገባ በድሬዳዋ ሲፈተን የዋለው የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ንግድ ባንክ ቡድን ክፍተት ባየባቸው ተጫዋቾች ምትክ ተጫዋቾችን ቀይሮ በማስገባት ክፍተቱን ለመድፈን ሲጥሩ የታዩ ቢሆንም ጠጣሩ የድሬዳዋ ከተማ የተከላካይ ክፍል ሚቀመስ አልነበረም፡፡ አጥቂዋ ትንቢት ሳሙኤል ባደረገችሁ አስቆጪ ሙከራ የቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ንግድ ባንክ ተሽሎ ቢታይም የምስራቁ ክለብ በሙከራ ረገድ ብልጫ ነበራቸው። 59ኛው ደቂቃ በረጅሙ ከመሀል ሜዳ የተላከን ኳስ የንግድ ባንኳ ግብ ጠባቂ ምህረት ተሰማ ስህተት ታክሎበት ፀጋነሽ ወራና አግኝታ ብትመታውም ለጥቂት ወጥቶባታል፡፡ድሬዳዋ ከተማዎች በሌላ አጋጣሚ በማዕድን ሳህሉ አማካኝነት ለጎል ቢቀርቡም ወደ ግብነት መለወጥ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ጨዋታው ሊጠናወው አስር ደቂቃዎች ሲቀሩት ንግድ ባንኮች በተሻለ ማጥቃት በድሬዳዋ ላይ ጫና ቢያሳድሩም በመከላከል ጥሩ አደራደር የነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ግብ ሳይቆጠርባቸው በመውጣት በመጨረሻም ጨዋታው ያለ ጎል 0-0 ተጠናቋል፡፡ ንግድ ባንኮችም ከአስር ጨዋታዎች የድል ጉዞ በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ማሸነፍ ሳይችሉ አቻ ወተዋል፡፡ ጨዋታው ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ክለቦቹ ሲያመሩ የንግድ ባንኳ አጥቂ ሎዛ አበራ በሜዳ ላይ እያለች የገጠማት ጉዳት ህመሙ እየተሰማት ሲመጣ በእንባ በህክምና ባለሙያዎች ድጋፍ ስትወጣ ተመልክተናል፡፡

-በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ያለው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛው ዙር ከጀመረ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑ ላይ ደርሷል፡፡ረፋድ አራት ሰአት ላይ በተደረገው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ላይ በሀዋሳ በአንደኛው ዙር የታየው እና ክለቦችም ሆኑ ዳኞች ወደ ሜዳ ሲገቡ በእግራቸው ኬሚካል እየረገጡ ወደ ሜዳ ሲገቡ የነበረበት መንገድ የኮቪድ 19 ቫይረስን ለመቀነስ እጅጉን የሚያስመሰግን ተግባር ቢሆንም ወደ ትሪቩን የሚገቡ ተመልካችም ሆኑ የውድድሩ አካል የሆኑት የቅድመ ጥንቃቄ የሙቀት መለኪያ የሚደረግላቸው ቢሆንም ከትሪቡኑ ውጪ ያሉ ተመልካቾች የኮቪድ ፕሮፖኮልን በጣሰ መልኩ ምርመራ ሳይደረግላቸው ወደ ስታዲየም ሲገቡ የታዩ ሲሆን ማስክም ሳያደርጉ ወደ ሜዳ መግባታቸው ሊታረም እና ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የድሬዳዋ ከተማዋን ተከላካይ ሀሳቤ ሙሶን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ