አምሳሉ ጥላሁን ጎል ካስቆጠረ በኋላ ያለቀሰበትን ምክንያት ይናገራል

ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ከተማን በረታበት ጨዋታ እጅግ አስደናቂ ጎል ያስቆጠረው አምሳሉ ጥላሁን በዕንባ ደስታውን የገለፀበት መንገድ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ይናገራል።

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ዓመት በአንፃራዊነት ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር አድርጎ የነበረው ፋሲል ከነማ የኃላ የኃላ የሚያቆመው ቡድን ጠፍቶ ተከታታይ ስድስተኛ ጨዋታውን በማሸነፍ በሊጉ አናት ላይ በመቀመጥ የዋንጫ ተገማች ቡድን ሆኗል። በዛሬው ዕለት በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ሀዋሳ ከተማን በረታበት ጨዋታ እጅግ አስደናቂ ጎል ያስቆጠረው አምሳሉ ጥላሁን ጎሉን ካስቆጠረ በኃላ በዕንባ የታጀበ የደስታ አገላለፅን አስመልክቶናል። ይህ ለምን ይሆን ስንል አምሳሉ ጥላሁንን ከጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ጠይቀነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

” ጎሉን አግብቼ ያለቀስኩት አራት ወንድሞቼ የምላቸው አብሮ አደጎቼን በሞት በማጣቴ ነው። ትንሽ የተወለድኩበት አካባቢ ባልተገባ ነገር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ወንድሞቼን በሞት በማጣቴ እነርሱን ለማሰብ ያለቀስኩት።

” ከዚህ በኃላ የሚያቆን የለም የቡድን መንፈሳችን አንድነታችን ከመቼውም ጊዜ በተለየ ተጠናክሯል። በየጨዋታው የማሸነፍ ፍላጎታችን ጨምሯል። በተከታታይ ስድስት ጨዋታዎችን ማሸነፋችን የበለጠ በስነ ልቦናው ጠንክረን እንድንገባ አድርጎናል።

” ባለፉት ዓመታት ደጋፊዎቻችንን የሊጉ ዋንጫ ለማንሳት ከፍተኛ ጥረት አድርገን አልተሳካልንም። ዘንድሮ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ጥሩ ቁመና ላይ እንገኛለን። በእያንዳንዱ ጨዋታ ሳንዘናጋ በትኩረት በመጫወት የዋንጫ እና ተከታታይ ጨዋታ የማሸነፍ ጉዟችንን እናስቀጥላለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ