የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ የመጀመርያ ዙር ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ኮልፌ እና መድን ማሸነፋቸውን ተከትሎ በአጓጊ ፉክክር የመጀመርያው ዙር ሲገባደድ በምድብ ለ አአ ከተማ ዙሩን በመሪነት ማጠናቀቁን አረጋግጧል።
ምድብ ሐ

ጠዋት 2:00 ላይ ማራኪ እንቅስቃሴ ያሳየው የባቱ ከተማ እና ስልጤ ወራቤ ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ጨዋታው በተጀመረ በ12ኛው ደቂቃ ባቱዎች በአንድ ሁለት ቅብብል ይዘው የገቡትን ኳስ ፍሬው ዓለማየሁ በቀላሉ አባከነው እንጂ መሪ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር። ኳስ በመቀባበል ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መግባት እና መቆየት ያልከበዳቸው ወራቤዎች የአደጋ ክልሉ ላይ ቢደርሱም ለግብ የደረሰ ሙከራ ሆነ ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በተሻጋሪ ኳስ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል የሚደርሱት ባቱዎች በበኩላቸው ለፈጣኑ እና ፈርጣማው አጥቂያቸው ፍፁም ዓለማየሁ የሚሻገሩ ኳሶች በመጠቀም የወራቤን የተከላካይ ክፍል ሲፈትሹ አርፍደዋል። በዚህም በ27ኛው ደቂቃ ወደ ሜዳ ተቀይሮ የገባው ያሬድ መሐመድ ከግራ መስመር ቃለአብ ጋሻው ያሻገረውን ኳስ የወራቤ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሙ ግሩም ኳስ አስቆጥሯል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደፊት መጓዝ ያልከበደው ወራቤ በአንድ ሁለት ቅብብል አጨዋወት በመውጣት ከቀኝ እና ከግራ መስመር ተሻጋሪ ኳሶች በመጠቀም በአማኑኤል ተፊሪ ሁለት የግንባር ኳሶች ሙከራ አድርጓል። መሪዎቹ ባቱዎች በመልሶ ማጥቃት በ44ኛው ደቂቃ መሪነቱን የሚሰፋበትን ዕድል ቢያገኙም መኳንንት አሸናፊ ቀድሙ በመውጣት አድኖባቸዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ስልጤ ወራቤ የመጀመሪያው 30 ደቂቃ እጅግ ብልጫን ወስደው መጫወት የቻሉ ሲሆን ባቱዎች በተቃራኒው በራሳቸው ሜዳ አፈግፍገው ተጫውተዋል። በዚህም በ58ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ገብረሚካኤል ያዕቆብ በግንባሩ በመግጨት ወራቤን አቻ የሚደርገውን ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ መነቃቃት የታየባቸው ወራቤዎች ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ ጫና መፍጠር ቢችሉም ውጤታማ አልነበሩም። በተቃራኒው በፍፁም ዓለማየሁ ጥረት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲደርጉ የነበሩት ባቱዋች በ74ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም አለማየሁ የግል ጥረቱን ተጠቅሙ ባቱን በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው 10 ደቂቃ ሲቀረው ውዝግቦች ማስተናገድ የጀመረው ሲሆን በ85ኛው ደቂቃ ተመስገን ዱባ ከርቀት በመታው ኳስ ወራቤዎች አቻ መሆን ችለዋል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የባቱ ቡድን መሪ ከወራቤው ወጌሻ ጋር አላስፈላጊ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው ታይተዋል። በተፈጠረው አጋጣሚም የባቱ አሰልጣኝ ወደስፍራው ያቀናውን የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተር ምስል የማስጠፋት እንዲሁም ድብደባ አድርሷል። በጨዋታውም በዳኝነት ላይ ቅሬታ አለን በማለት በዛው ደቂቃ ክስ አስይዘው ጨዋታው በ2-2 አቻ ውጤት ተጠናቋል።

4:00 ላይ ኮልፌ ክ/ከተማ የካን 2-1 አሸንፎ ነጥቡን ከመሪው አርባምንጭ ጋር አስተካክሏል። ማራኪ እና የአካል ንክኪ ያልበዛበት እንቅስቃሴ ያስመለከተን ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በነበረ ከፍተኛ ጨዋታውን በበላይነት ለማጠናቀቅ የነበረ ጥረት ታይቶበት ተከናውኗል። በጨዋታው የተሳካ የኳስ ቅብብሎች ያስመለከቱት ኮልፌዎች ከተጋጣሚያቸው እጅጉን በተሻለ መልክ የግብ ክልል እየደረሱ ጥቃት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል። በተቃራኒው የካዎች ተለዋዋጭ የጨዋታ ቅርፅ በማሳየት በረጅሙ የሚጣሉ እንዲሁም በአጭር ቅብብል ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመሄድ ጥቃት መፈፀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ4ኛው ደቂቃ አንዋር ዱላ አክርሮ በመታው የግብ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ኮልፌዎች በመጀመሪያው ሀያ ደቂቃዎች ለሦስት ጊዜ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን የሁለተኛ ሙከራው ሙሉአለም በየነ በግንባሩ የገጨው ኳስ ወደ ግብነት ተለውጧል። የካዎች ተከላካዩች በሚሰሩት ጥቃቅን ስህተት ምክንያት ጫና ውስጥ ቢወድቁም የአማካይ ክፍላቸው ጥንካሪ ሊመሰገን ይገባል። በተለይም ከመስመር ላይ ወደ ውስጥ በሚጥሉት ኳሶች በግዙፋ አጥቂቸው ቢንጃሚን ለመጠቀም ጥረት ሲደርጉ ቆይተዋል። ይህም ጥረታቸው በ23ኛው ደቂቃ ሰምሮላቸው ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ቤንጃሚን በግንባሩ በማስቆጠር አቻ ሆነዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ መነቃቃት የታየባቸው የካዋች ንጉሱ ጌታሁን የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ያዳነው እንዲሁም በ37ኛው ደቂቃ በረጅሙ ተሻግሮ ያገኝውን ኳስ ክብረአብ ማቱሳላ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ፊት በመግባት ወደ ግብ የሚለወጥበትን እና ቡድኑን መሪ ማድረግ የምትችል መልካም ዕድል በቀላሉ አምክነዋል።

ኮልፌዎች ከሁለቱም መስመር ተሻጋሪ ኳሶች እንዲሁም ከቅርብ ርቀት ላይ ሆነው የሚገኙትን የቆሙ ኳሶች ወደ ግብ መቀየር ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ወደ ራሳቸው እንቅስቃሴ የተመለሱት የካዎች በረጃጅም ኳሶች እና ከቆሙ ኳሶች የተጋጣሚያቸውን መረብ ለመጎብኘት ቢጥሩም ዕድሎችም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኳሱን በእርጋታ የሚያሽከረክሩ የነበሩት ኮልፊዎች ከቀኝ እና ግራ መስመር በፍጥነት ወደ ሳጥን በመግባት ጥቃት በመሰንዘር ጥቃት ቢፈፅሙም ረዘም ላለ ደቂቃ በአጥቂዎቻቸው ስህትተ ስኬታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። 

በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ሲያመሩ የነበሩት ኮልፌዎች የማታ ማታ በፍጥነት ወደፊት ያሻገሩት ኳስ ሀይደር ዳዋሙ ይዞት ሲገባ ፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ በተሰራ ጥፋት የተገኛውን እድል ፈቱ አብደላ ወደ ግብነት ለውጦታል። ረጃጅም ኳሶች በመጣል ጥቃት መፈፀም ላይ ያዘወተሩት የካዋች በ77ኛው ደቂቃ ኪሩቤል ከቀኝ መስመር በግል ጥረቱ ይዞት የገባውን ኳስ በቀላሉ ካበከነው በተጨማሪ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ እዮብ ካሳዬ አክርሮ የመታው ኳስ ከግብ ጠባቂው ቢያልፍም በተከላካይ ጥረት ከግብነት ድኗል። አስደንጋጭ የግብ ሙከራ ባላስመለከተው ጨዋታ የካዎች መጨረሻዋቹ ደቂቃዎች ላይ እጅጉን ተጭነው ቢጫወቱም እድል ሳይቀናቸው ቀርቶ ጨዋታው በኮልፌ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

9:00 ላይ ኢትዮጽያ መድን ደቡብ ፖሊስን 1-0 አሸንፎ ወደ መሪዎቹ ተጠግቷል። እጅግ አሰልቺ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች ይህ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳንመለከት ተጠናቋል። በ5ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ቶማስ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ መሐመድኑር ናስር በቀጥታ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መትቶ ወደውጪወጣበት የመድን ብቸኛ የአጋማሹ ሙከራ ሲሆን ኤርሚያስ ደጀኔ ከርቀት መትቶ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ያዳነበት በተመሳሳይ የደቡብ ፖሊስ ብቸኛ ሙከራ ነበር።


በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች መድኖች የተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ በብርሃኑ ቦጋለ፣ መሐመድኑር ናስር እና ኤፍሬም ቶማስ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ እድሎችን መፍጠርም ችለዋል። በ64ኛው ደቂቃም በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ የደቡብ ፖሊሱ ፍፁም ተስፋዬ በእጁ በመንካቱ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት በተረጋጋ ሁኔታ የመታው ኤፍሬም ቶማስ ወደ ግብነት በመለወጥ የመድን ብቸኛ የማሸነፊያ ግብን አስቆጥሯል።

ምድብ ለ

አዲስ አበባ ከተማ መራነቱን ያጠናከረበትን ውጤት ካፋ ቡናን 1-0 በማሸነፍ አሳክቷል። ሰዒድ ሰጠኝ በ79ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል የመዲናይቱ ክለብ መሪነቱን በሰባት ነጥብ ልዩነት እንዲይዝ አስችሎታል።

ሀምበሪቾ ሶዶ ከተማን 3-0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጓል። የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል በተጠናቀቀው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ፀጋአብ ዮሴፍ፣ ዳግም በቀለ እና ታምራት ስላስ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ሀምበሪቾን ለድል አብቅተዋል።

በምድቡ ሌላ ጨዋታ ጋሞ ጨንቻ ከ አቃቂ ቃሊቲ ያለ ጎል ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።

የምድብ ለ የዘጠነኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች በመጪዎቹ ቀናት ከተካሄዱ በኋላ የመጀመርያው ዙር የሚጠናቀቅ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ