የባህር ዳር ዝግጅት ወቅታዊ መረጃዎች

ለቀጣዮቹ 22 ቀናት የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስተናጋጅ የሆነችው ባህር ዳርን ቅድመ ዝግጅት የተመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲህ አቅርበንላችኋል።

በቤት ኪንግ ስም የተሰየመው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተለየ የውድድር አካሄድ ቀጥሎ ሦስተኛ አስተናጋጅ ከተማው ላይ ደርሷል ፤ ባህር ዳር። ከኮቪድ 19 መከሰት አስቀድሞ የካቲት 29 2012 ላይ ባህር ዳር ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን ካስተናገደበት የዐምናው 16ኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ ከተማዋ ነገ ረፋድ ላይ በወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ ይከናወንባታል። ከአዲስ አበባ እና ጅማ በመቀጠል ዕንግዶችን የተቀበለችው ባህር ዳር ከሁለቱ አዘጋጅ ከተሞች በተወሰደ ልምድ በተሻለ ሁኔታ ውድድሩን እንደምታስኬድ ይጠበቃል። ዛሬ ላይ የተመለከትናቸው ሁኔታዎችም ይህንን የሚጠቁሙ ሆነዋል።

* ከተማዋ በተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ ላይ የምትገኝ ሲሆን በግዙፉ የባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታድየም ዙሪያም በቂ ጥበቃ ሲደረግ ተመልክተናል።

* በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች ተጠቃለው ወደ ባህር ዳር ገብተዋል። ምንም ዕረፍት ሳይሰጥ የቆየው ድሬዳዋ ከተማ በቅድሚያ የደረሰ ክለብ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ በትናንትናው ዕለት ወደ ከተማዋ መጥቷል።

* የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማህበር ከአየር ማረፊያ ጀምሮ አቀባበል በማድረግ ተሳታፊ ክለቦች ባረፉባቸው ሆቴሎች በመገኘት ጭምር ሰፋ ያለ እና የአካባቢውን ባህል የሚያስተዋውቅ የአቀባበል ሥነ-ስርዓት አከናውኗል።

* የባህር ዳሩ ውድድር በሜዳ ዝግጅት ረገድ የተለየ ከፍታን እንደሚያስመለክተን ይጠበቅ የነበረ ሲሆን ውድድሩ በሚካሄድበት የባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታድየም ተገኝተን የተመለከትነውም ይህንን ነው። መጫወቻ ሜዳው እጅግ በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ አረንጓዴ ሆኖ እና የተኛውም ቦታ ላይ የመጎዳት ምልክት ሳይታይበት የውድድሩን መጀመር እየተጠባባቀ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም ስድስት የልምምድ ሜዳዎች ተወዳዳሪ ቡድኖች ዝግጅቶቻቸውን እንዲያከናውኑባቸው የተዘጋጁ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

* የሊግ ካምፓኒው ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፉ እና የሊግ ካምፓኒው የውድድር ሰብሳቢ ዶ/ር ተገኔ ዋልተንጉስ የውድድሩ የበላይ መሪ በመሆን ወደ ባህር ዳር መጥተዋል።

* የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ እንደ ጅማው ውድድር ሁሉ አስራ ሦስት ዋና እና አስራ ሦስት ረዳት ዳኞችን በመያዝ ባህር ዳር ደርሷል። ከዚህ በተጨማሪም ብቸኛዋን እንስት ተስፋነሽ ወረታውን ጨምሮ ሰባት የጨዋታ ታዛቢዎች በከተማዋ ተገኝተዋል።

* ውድድሩን በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የሚያስተላልፈው ሱፐር ስፖርት 28 አባላት ባህር ዳር ደርሰዋል። የተቋሙ ማሰራጫ ጣቢያዎችን የያዙት ተሽከርካሪዎችም በስታድየሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ ቆመው ተመልክተናል። በጅማው ውድድር በተንታኝነት የሰነበተው ኃይለእግዛብሔር አድሀኖምን ጨምሮ ሰዒድ ኪያር ፣ አወቀ አብርሀም እና መኮንን ኃይሉ በአማርኛ ስርጭት ሽፋን ለመስጠት ከቦታው ተገኝተዋል።